ሰኔ 19/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት የአፍሪካ ቀንድ ትንታኔ!
በሱዳን ከሁለት ዓመታት በላይ በዘለቀው አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት በቀጠናው ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ እየከፋ መጥቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከኬኒያ ሞምባሳ ወደብ ወደ ሱዳን የሚጓጓዘው የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የጦር መሣሪያ መተላለፊያ መሆኗን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የሚውል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) የጦር መሳሪያ መተላለፊያ በር መሆኗ በሱዳን ያለውን ግጭት ከማባባስ ባሻገር፣ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ቀጠናዊ ውጥረት የሚያባብስ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሱዳን ውስጥ በጄኔራል ሞሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) በገንዘብና በወታደራዊ ግብዓት እየደገፈች እንደሆነ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና የጥናት ተቋማት ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህ ድጋፍ የRSFን ወታደራዊ አቅም በማጠናከር ጦርነቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ በርካታ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከአቡዳቢ ጎን መሰለፉ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።
የኬኒያው ሞምባሳ ወደብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የጦር መሳሪያ የምታስተላልፍበት ዋነኛ መግቢያ በር እየሆነ ስለመምጣቱ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለመፅሔታችን ገልጸዋል። ይህ የጦር መሳሪያ ከሞምባሳ ተነስቶ በኢትዮጵያ ግዛት በኩል አልፎ ወደ ሱዳን ይደርሳል።
ለአብነት ያህል ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ከሞምባሳ ወደብ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በርካታ የጦር መሳሪያ በኢትዮጵያ በኩል አልፎ ሱዳን መድረሱን ዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል። ሁኔታው አቡዳቢ የኢትዮጵያን ድንበር በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ላላት ተሳትፎ እንደ ቁልፍ መተላለፊያ መስመር እየተጠቀመችበት መሆኑን ያመላክታል።
ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ጥብቅና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት መመስረታቸው የሚታወቅ ነው። የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካ በንቃት የሚከታተሉ ተንታኞች የሁለቱ ሀገራት ጥብቅ ቁርኝት አቡዳቢ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ፍላጎት ለማሳካት ኢትዮጵያን እንደ ስትራቴጂካዊ መተላለፊያ እየተጠቀመች ስለመሆኗ ሲገልፁ ይስተዋላል።
የዚህ ግንኙነት ጥልቀት በግልጽ የታየው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ልዑል አልጋወራሽ ሼክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ በፈረንጆቹ ነሐሴ 2023 ዓ.ም ኢትዮጵያን በይፋ በጎበኙበት ወቅት ነበር። በጉብኝቱ ወቅት ሁለቱ ሀገራት የሰላምና ጸጥታ ዘርፍን ጨምሮ በ17 የተለያዩ ዘርፎች ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ይህ ክስተት የተባበሩት አረብ ኢምሬትን ተጽዕኖ በአፍሪካ ቀንድ ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞችና ምሁራን የሚስማሙበት ሲሆን፣ ሁኔታው በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እና በሌሎች ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እየሰፋ ያለውን የአቡዳቢ መንግሥት ተፅዕኖ በጉልህ ያሳያል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አንደኛውን ወገን በመደገፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረገች ነው የሚሉ ክሶች ቢቀርቡባትም፣ አቡዳቢ እነዚህን ውንጀላዎች በተደጋጋሚ ስታስተባብል ትደመጣለች።
ይሁን እንጂ በቅርብ ጊዜ በተፈጠረ ተያያዥ ክስተት፣ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርቱም በሚገኘው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘን ውስጥ የኬንያ ማህተም ያረፈባቸው በርካታ የጦር መሳሪያዎችን እና ተተኳሾችን ማግኘታቸውን በመግለጽ፣ በያዝነው ሳምንት በኬንያ መንግሥት ላይ ክስ አቅርበዋል።
ከኬኒያው ሞምባሳ ወደብ ተጭኖ ወደ ሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኢትዮጵያ ድንበር አልፎ ስለሚደርሰው የጦር መሳሪያ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያጋሩት ምንጫችን፣ “ለተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበሮች ምቹ መተላለፊያ ሆኖላቸዋል” በማለት ጉዳዩን አብራርተዋል።
ይህ ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት እና የቀጠናውን ደኅንነትን በሚመለከት ሰፊ አንድምታዎች የሚኖረው ሲሆን፣ ጦርነቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት የጦር መሳሪያ አቅርቦትን በተመለከተ የሚነሱት ውንጀላዎች በቀጠናው ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ያደርጉታል።


