ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
የፌዴራል መንግሥቱ “የትግራይ ጄኔራሎች ተላልፈው ይሰጡኝ” ሲል በትናንትናው ዕለት ከትግራይ ክልል መሪዎች ጋር በመቀሌ ከተማ ውይይት ባደረገው የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ልዑክ በኩል ጠይቋል።
ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ ወደ መቀሌ ያቀናው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ልዑክ፣ ከዐቢይ አህመድ መንግሥት ስምንት ነጥቦችን የያዘ መልዕክት ይዞ መጓዙን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህ ነጥቦች መካከል፣ በሕገወጥ የማዕድን ማውጣት እና የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ እንዲሁም ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል ያላቸውን የትግራይ ጀነራሎች ተላልፈው እንዲሰጡኝ ሲል የፌዴራል መንግሥቱ መጠየቁን ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ከህወሓት ወጥተው ስምረት ፓርቲን የመሰረቱት እና የጠቅላይ ሚንስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ባሳለፍነው ግንቦት ወር የመንግሥት ልሳን ከሆነው ፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ “በሕገወጥ የወርቅ ንግድና የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ የህወሓት ጄኔራሎች የትግራይን ሕዝብ ሰላም እየነሱት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ህውሓት ሕጋዊ ሰውነት የሌለው ፓርቲ በመሆኑ ከየትኛውም አይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲቆጠብ፣ ከግዚያዊ አስተዳደሩ ሕገወጥ ተሳትፎው እንዲወጣና ማህተም እንዲያስረክብ፣ ተፈናቃዮችን በማስመለስ ስም የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲተው፣ እንዲሁም የትግራይን ታጣቂዎች የሚያደራጁ ወታደራዊ አመራሮች በጡረታ እንዲሰናበቱ መጠየቁን የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።
ይሁንና፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት በሚከተለው የጦርነት ፖሊሲ ምክንያት እና የህወሓት ጄኔራል ታጣቂዎችን መልሶ ወደማደራጀት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው፣ ሌላ ዙር ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል በርካቶች አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ወደ መቀሌ ተጉዞ ከትግራይ ክልል መሪዎች ጋር ውይይት ካደረገው የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ተያይዞ፣ “ጉባኤው የዐቢይ አህመድ መንግሥት ፍላጎት ማስፈፀሚያ ተደርጓል” የሚሉ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች በበርካቶች ይነሱበታል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ በደሎችን በዝምታ እየተመለከተ በአንፃሩ ግን የዐቢይ አህመድ መንግሥት ፍላጎቱን ለማስፈፀም የጉባዔውን ድጋፍ በሚፈልግበት ጊዜ ጉባኤው በተደጋጋሚ የሚሰጣቸው አፋጣኝ ምላሾች በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ወቀሳ እንዲነሳበት የሚያደርጉ ምክንያቶች ናቸው።


