ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰመስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አጎራባች የሆነው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ከሰሞኑ ያሳለፈውን መዋቅራዊ ውሳኔ በማስመልከት ካቢኔያቸውን ለውይይት ሊጠሩ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የሶማሌን እና ኦሮሚያ ክልሎችን ሲያወዛግቡ የነበሩ ሞያሌን ጨምሮ በርካታ ወረዳዎችን ወደ ሶማሌ ክልል መዋቅር ለማጠቃለል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነው አቶ ሽመልስ አብዲሳ ካቢኔያቸውን ይጠራሉ የተባለው።
የሶማሌ ክልል የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሳባቸው የነበሩትን ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚያዋስኑትን ወረዳዎች በምክር ቤቱ በኩል ወደ ሶማሌ ክልል መዋቅር ለማጠቃለል መወሰኑን ተከትሎ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ለመምከር ስብሰባ ሊቀመጥ ኒውስ።
አቶ ሽመልስ አብዲስ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ውሳኔን በማስመልከት የክልላቸውን የልዩ ኃይል እና የፖሊስ እንዲሁም የሠላምና ደኅንነት ኃላፊዎችን ጨምሮ በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች የተመደቡ የክልልና የዞን የፖለቲካ አመራሮችን ጠርተው እንደሚያነጋግሩ ለማወቅ ተችሏል።
ርዕሰመስተዳድሩ ጥሪ ከሚያቀርቡላቸው አመራሮች መካከል የኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር የሚያዋስኑ ዞኖችን የሚመሩ የፀጥታና ፖለቲካ ዘርፍ አመራሮች የሚገኙበት ሲሆን፣ አመራሮቹ የየዞኖቹን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ሪፖርት እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውንም ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ቦረና እና ጉጂ ዞኖች የኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር የሚያዋስኑ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል ተደጋጋሚ የድንበር አካባቢ ግጭቶች፣ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች፣ እና የግብርና መሬትና የውሃ መብት ጥያቄዎች ሲያስተናግዱ መኖራቸው አይዘነጋም።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከክልል እንዲሁም ከዞን የፀጥታ እና ፖለቲካ አመራሮች በተጨማሪ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ብልፅግና አመራሮቹንም ጠርተው እንደሚያነጋግሩ የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።
ዞብል ፖስት “አቶ ሽመልስ አብዲሳ ካቢኔያቸውን ጠርተው ለማነጋገር ቀጠሮ የያዙት ለመቼ ነው?” የሚል ጥያቄ ለመረጃ ምንጫችን ያቀረበ ቢሆንም፣ የመረጃ ምንጫችን ከጉዳዩ ባሻገር ዕለቱን በርግጠኝነት እንደማያውቁት ለመጽሔታችን አስረድተዋል።


