ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ጋዜጠኞችን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ሀገር ቤት የሚወስድ ኃይል ማቋቋሙን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የተቋሙ የመረጃ ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
የዐቢይ አህመድ መንግሥት በተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ይሳተፋሉ ያላቸውን የሚዲያ ባለሙያዎችን አስሮ ወደ ኢትዮጵያ ለመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚጠቁሙ መረጃዎች በተለያዩ ጊዜያት መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ ተግባር ለመግባት ስራ እንደተጀመረ ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
የፌደራል ፖሊስ በውጭ ሀገራት በስደት የሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎችን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ይዞ ወደ ሀገር ቤት ለመውሰድ ያዋቀረው ቡድን፣ የደኅንነት እና የልዩ ኦፕሬሽን አባላትን ያቀፈ መሆኑን መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት የተቋሙ ምንጮች ገልጸዋል።
ግብረኃይሉ ስምሪት የሚያደርገባቸው ሀገራት ከመካከለኛው ምስራቅ የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች፣ ከአፍሪካ ደግሞ ኬኒያ እና ዩጋንዳ መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፌደራል ፖሊስ ምንጫችን አያይዘው ጠቁመዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መንግሥት የፌድራል ፖሊስ ግብረኃይሉን ከሚያሰማራቸው ሀገራት ጋር የዲፕሎማሲያዊ፣ የፀጥታ፣ እና የደኅንነት ስምምነቶችን ማድረጉን የዞብል ፖስት ምንጮች ያደረሱት መረጃ ያሳያል።
በዱባይ፣ ኬኒያ፣ እና ዩጋንዳ የተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ አውታሮችን ተጠቅመው በጋዜጠኝነት እና የሚዲያ ሙያ የተሰማሩ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለተቀረው ዓለም በማጋለጥ የሚታወቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን፣ መንግሥት እነዚህን ሙያተኞች በሀገር ክህደት እንዲሁም በደረቅ ወንጀል ለመክሰስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን መጽሔታችን አረጋግጧል።
ለዚህም ያመች ዘንድ ለክስ የሚሆኑ የተለያዩ ሰነዶችን የሚያዘጋጅ የፌደራል ፖሊስ ወንጀለ ምርመራ ዘርፍ እና አቃቤ ሕግ የተጣመሩበት ቡድን የተቋቋመ ሲሆን፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የሚዲያ ሙያተኞችን ለመያዝ ከተቋቋመው ግብረኃይል ጋር በጋራ እንዲሰሩ አቅጣጫ መሰጠቱ ተነግሯል።
የፌደራል ፖሊስ የመረጃ ምንጮች ለዞብል ፖስት ያደረሱት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በተጠቀሱት ሀገራት የሚገኙ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ከመስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ በቁጥጥር ስር ለማዋል እቅድ መያዙንና ፍርድ ቤቶች ስራ ሲጀምሩ ተቀዳሚ ሃላፊነታቸው ይሄንን ጉዳይ መመልከት ይሆናል ተብሏል።
የፌደራል ፖሊስ ደኅንነትና ልዩ ኦፕሬሽን አባላቶችን ያቀፈው ግብረኃይል ስምሪት በሚያደርግባቸው ሀገራት የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎች እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን፣ የመንግሥትን የጦርነትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚተቹ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ግፎችን የሚያጋልጡ ሙያተኞች ዋነኛ ዒላማ እንደሚሆኑ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኃላፊ የሆኑትን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን እና ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ፣ የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት የፌደራል ፖሊስ ግብረኃይል ይሰማራባቸዋል ከተባሉ ሀገራት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው አይዘነጋም።
በተጠቀሱት ሀገራት በርካታ የአማራ ተወላጅ የሚዲያ ባለሙያዎች የሚገኙና በአማራ ሕዝብ ላይ የታወጀውን ጦርነት ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው የጦርነት ዘገባዎችን እና የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን ለሕዝብ እንደሚያደርሱ የሚታወቅ ሲሆን፣ እኒሁ የአማራ ተወላጆች ቀዳሚ ዒላማ እንደሚሆኑ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከዚህ ቀደም በርካታ የአማራ ተወላጅ ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ እንዲሁም የፌድራል፣ የአዲስ አበባ፣ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕዝብ ተወካዮችን በገፍ ማሰሩ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የስርዓቱን ግፍ ሸሽተው በስደት ላይ ሚገኙ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለማሰር የጀመረው እንቅስቃሴ የስርዓቱን ጭካኔ እና አምባገነንነት ይበልጥ አጉልቶ የሚያሳይ ይሆናል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በፌድራል ፖሊስ የልዩ ኦፕሬሽን እና ደኅንነት አባላት ከጅቡቲ ተያዞ ለእስር መዳረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ መንግሥት በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ዝግጅት መጀመሩ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።
በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ይደረጋሉ ከተባሉት የሚዲያ ሙያተኞች ውስጥ፣ በሳተላይት ቴሌቪዥን፣ ዩትዩብ፣ በይነ-መረብ፣ እና ቲክቶክ መረጃዎችን ለሕዝብ የሚያደርሱ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በመንግሥት ዒላማ እንደሚደረጉ ከፌዴራል ፖሊስ በደረሰን መረጃ መሰረት ለማወቅ ተችሏል።
ኢትዮጵያ የመናገር ነፃነትን በማፈን እና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም ዓለም ላይ ቀዳሚ ከሆኑት ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ ይሄኛው የመንግሥት ውሳኔ ሲታከልበት ነገሮችን የከፋ ደረጃ ላይ እንደያደርስ ይጠበቃል።


