Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየኢትዮጵያ መንግሥት አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ እያካሄደ መሆኑ ተነገረ።

የኢትዮጵያ መንግሥት አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ እያካሄደ መሆኑ ተነገረ።

ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!

የዐቢይ አህመድ መንግሥት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ እና አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ እያካሄደ እንደሚገኝ የዐይን እማኞች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።

በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በቀጠለው አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በስፋት እየተካሄደ ስለመሆኑ ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያመላክታል።

ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ በነሐሴ ወር ብቻ ሦስት ጊዜ ወታደራዊ አፈሳ የተካሄደ ሲሆን፣ ያሳለፍነውን ቅዳሜ እና እሁድ ጨምሮ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች እና አመራሮች ቅዳሜና እሁድን እየጠበቁ መታወቂያ የሌላቸውን፣ የቀን ሠራተኞችን እና ጎዳና ተደዳሪዎችን በጅምላ የማፈስ እና ወደ ማቆያ ስፍራዎች የመውሰድ ተግባር በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት የዐይን እማኞች አስረድተዋል።

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ታፍሰው የተወሰዱት በርካታ ወጣቶች በአሁኑ ሰዓት ከቃሊቲ ውሃ ልማት ጀርባ በሚገኘው የቀድሞው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚንስቴር መጋዝን ውስጥ በጅምላ ታስረው እንደሚገኙ የዐይን እማኞች ለመጽሔታችን ገልጸዋል።

በአስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ በጅምላ የተያዙት ወጣቶች የታሰሩበት መጋዝን ከዚህ ቀደም የዐቢይ አህመድ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት መክፈቱን ተከትሎ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የአማራ ተወላጆች በጅምላ ታስረውበት የነበረ ቦታ መሆኑን የመረጃ ምንጫችን አያይዘው ገልጸዋል።  

በተመሳሳይ በአማራ ክልልም አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን በወልዲያ፣ ቆቦ፣ ላሊበላ፣ ግዳን፣ ቡግና፣ ላስታ፣ ሐይቅ፣ እና ደሴ አካባቢዎች በርካታ ዜጎች ተይዘው ወደ እስር ቤቶች መወሰዳቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል። 

በአማራ ክልል ጅምላ ከታፈሱት ሰዎች መካከል ከገጠር ለገበያ የመጡ ገበሬዎች፣ የጉልበት ሠራተኞች፣ እንዲሁም የክልሉ መንግሥት የሚሊሻ አባላት ጭምር እንደሚገኙበት ዞብል ፖስት በጅምላ ከታፈሱ ዜጎች የቤተሰብ አባላት ያገኘው መረጃ ያሳያል።

በኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ ተመሳሳይ የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ መካሄዱ የተነገረ ሲሆን፣ በናዝሬት፣ ጅማ፣ እና ሻሸመኔ ከተሞች ወጣቶችን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ እና የቀን ሠራተኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች የጅምላ አፈሳ ሰለባ መሆናቸው ተነግሯል።

በቀጠለው መጠነ ሰፊ እና አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ በተለያዩ ማጎሪያ ቦታዎች በጅምላ እንዲቆዩ የተደረጉት ዜጎች በቀጣይ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እንደሚወሰዱ እና የውትድርና ስልጠና እንደሚሰጣቸው ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጮች ለዞብል ፖስት ያደረሱት መረጃ ያሳያል።

የዐይን እማኞች የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳው በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄደ እንደሚገኝ የጠቆሙ ቢሆንም፣ በሌሎች የሀገሪቷ አካባቢዎችም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ይገመታል።

የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከዚህ በፊት ለውትድርና ብቁ ያልሆኑ ህፃናትን እና የአዕምሮ ጤና እክል ያለባቸውን ዜጎች ጭምር በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ወታደራዊ ስልጠና ጣቢያዎች መውሰዱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ የዓለምአቀፍ ተቋማት እና መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ማጋለጣቸው አይዘነጋም።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች