Thursday, May 7, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮች"የኃይማኖት አባቶችን መግደል ያልተፃፈ ሕግ ሆኗል" እናት ፓርቲ!

“የኃይማኖት አባቶችን መግደል ያልተፃፈ ሕግ ሆኗል” እናት ፓርቲ!

ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና! 

እናት ፓርቲ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኃይማኖት አባቶች ላይ እየተፈፀመ ያለውን አሰቃቂ ግድያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “የኃይማኖት አባቶችን መግደል ያልተፃፈ ሕግ ሆኗል” ሲል ገልጿል።

እናት ፓርቲ ባወጣው የሀዘን መግለጫ በነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን፣ ሮቤ ወረዳ፣ መሰራንጄ አቦ የሚገኘው የኦዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት የ78 ዓመት አረጋዊ ካህን ንጉሴ ወልደ መድኅን በቤታቸው እያሉ በታጣቂዎች በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን አስታውቋል።

ፓርቲው በዛሬው ዕለት ባወጣው የሀዘን መግለጫ እንደተመለከተው ባለፉት ሰባት ዓመታት ታላላቅ የኃይማኖት አባቶችን እያደኑ መግደል እና ግድያውን ማዳፈን ዋና ተግባር ሆኗል በማለት በኃይማኖት አባቶች ላይ የሚፈፀመውን ግድያ ኮንኗል።

እናት ፓርቲ በመግለጫው አያይዞም “ኦሮሚያ ክልል በተለይ አርሲ ዞን የደም መሬት ሆኗል” በማለት በአካባቢው በኃይማኖት አባቶች ላይ የሚፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ የገለፀው ሲሆን፣ በአርሲ ዞን መግሥትም መንግሥታዊ መዋቅርም የሌለበት እስኪመስል በኃይማኖት አባቶች ላይ ተደጋጋሚ አሰቃቂ ግድያ እየተፈፀመ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፓርቲው መግለጫ እንደሚጠቁመው በአርሲ ዞን የተለያዩ አካባቢ በኃይማኖት አባቶች ላይ እጅግ በተጠና መልኩ በየጊዜው አሰቃቂ ግድያ እና እገታ የሚፈፀም ሲሆን፣ ድርጊቱ የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል። ይሁን እንጅ መሰል አሰቃቂ ግድያዎችን የሚፈፅሙ አካላት ማንነት እና ተልዕኮ እስካሁን በግልፅ ሊታወቅ አልቻለም።  

በተመሳሳይ ግድያ በነሐሴ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የጎጆ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የድጓ መምህር የሆኑት መምህር አፈወርቅ አበባው ምሽት 1 ሰዓት ላይ በተለምዶ ጣፎ አደባባይ፣ ገደራ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደቤታቸው በመጓዝ ላይ እያሉ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን እናት ፓርቲ ከሟች ቤተሰብ ማረጋገጡን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች