መስከረም 6/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ “ክልሉን ከመከላከያ ሠራዊቱ ለመረከብ የሚያስችል አቅም ለመገንባት መስራት አለብን” ማለታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ይህንን ያሉት በትናንትናው ዕለት የአማራ ክልል ፀጥታ ምክር ቤት የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ ለመገምገም በተሰበሰበበት ወቅት ነው ተብሏል።
በአቶ አረጋ ከበደ የተተኩት የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በሐምሌ 27/2015 ዓ.ም የፌዴራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊቱን በአማራ ክልል እንዲያሰማራ በደብዳቤ ከጠየቁበት ጊዜ አንስቶ የአማራ ሕዝብ በከፋ ጦርነት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
አቶ አረጋ የሚመሩት የአማራ ክልል መንግሥት የክልሉን በጀት ሙሉ በሙሉ ለጦርነት በማዋል 25 ሺህ የሚጠጋ የአድማ ብተና እና ሚሊሻ ኃይል በማሰልጠን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ርዕሰ-መስተዳድሩ ክልሉን ከመከላከያ ለመረከብ አቅማችንን እናጠናክራለን ያሉት ይሄንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ተብሏል።
በርካታ የአድማ ብተና እና ሚሊሻ ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኘው የፌዴራል መንግሥቱ “መከላከያ ሠራዊቱ ክልሉን ለቅቆ እንዲወጣ” ቢወሰን ክልሉን አቶ አረጋ ከበደ የሚመሩት መንግሥት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እንዲቻል በማሰብ ነው ተብሏል።
ሁለት ዓመታትን ባስቆጠረው ጦርነት፣ በከባድ መሳሪያ እና በአየር ድብደባዎች እንዲሁም ቤት ለቤት በተፈፀሙ ግድያዎች በርካታ ንፁሐን ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት መውደሙን፣ የኢኮኖሚ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ እና ሌሎች ማህበራዊ እንቅስቅሴዎች መስተጓጎላቸውን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የቀድሞው ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ አማራ ክልል እንዲገባ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ተከትሎ፣ በቀድሞው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኃላፊ በአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሐምሌ 28/2015 ዓ.ም መታወጁ የሚታወስ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው የሚመሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ2016 ዓ.ም በጥር ወር መጨረሻ ላይ ድጋሚ ለአራት ወራት መራዘሙ አይዘነጋም። ከዚህ ጊዜ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መልሶ ባያራዝመውም፣ የአማራ ሕዝብ ዛሬም ድረስ አገልግሎት ላይ እየዋለ በሚገኝ እና በአራት ዕዞች በተዋቀረ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚመራ ጦርነት እንደተከፈተበት የብዙዎች ዕምነት ነው።
የአማራ ክልልን ከመከላከያ ሠራዊት ለመረከብ እየሰራን ነው ያሉት አቶ አረጋ ከበደ ባሳለፍነው ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ “ክልሉን ለመቆጣጠር በምናደርገው ጥረት ጥሩ አፈፃፀም አስመዝግበናል” ሲሉ በሪፖርታቸው መጥቀሳቸውን እና “ፋኖን ሙሉ በሙሉ እስክናሸንፍ ጦርነቱ ይቀጥላል” የሚል አቋም እንዳላቸው መዘገባችን አይዘነጋም።።
በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ጉዳቶች እየደረሱ የሚገኝ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት ጦርነቱን አስቀጥላለሁ የሚለው አቋሙ ደግሞ ሕዝቡ እያስተናገደ የሚገኘውን ጉዳት የበለጠ የከፋ ያደርገዋል ተብሎ ይታሰባል።
ከዚህ አንፃር አቶ አረጋ ከበደ በሚመሩት የአማራ ክልል መንግሥት “ጦርነትን ማራዘም ፋኖ አለው ተብሎ የሚታሰበውን ሕዝባዊ ቅቡልነት ማሳጣት የሚቻልበት አንድ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልት ተደርጎ እየተወሰደ ነው” ሲሉ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልፀዋል።
በሌላ በኩል፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚገኙ የፋኖ ኃይሎች ወጥ ድርጅታዊ መዋቅር ለመፍጠር አለመቻላቸው ጦርነቱን ከአማራ ክልል ለማስወጣት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል የሚሉ ጠንካራ ትችቶች እና አስተያየቶች ከተለያዩ ወገኖች በመደመጥ ላይ ይገኛል።
ይሄንን ተከትሎ ከዐቢይ አህመድ የጦርነት ፖሊሲ ባሻገር የፋኖ ኃይሎች አንድነትን ለማምጣት አለመቻል ሁለት ዓመታትን የተሻገረው የአማራ ጦርነት ወደ ሦስተኛ ዓመቱ እንዲሄድ እና የአማራ ሕዝብ በተራዘመ ጦርነት እንዲቆይ እየተደረገ እንደሆነ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ ይደመጣሉ።
ከዚህም በተጨማሪ፣ የፋኖ ኃይሎች አንድ ወጥ መዋቅር ለመመስረት አለመቻላቸው ክልሉ የገጠመውን ቀውስ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በኅብረተሰቡ ላይ እገታ እና ዝርፊያ ለሚፈፅሙ ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው የፖለቲካ ተንታኞች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ሁኔታውን አስመልክቶ በሚያጋሩት ሃሳብ የጉዳዩን አሳሳቢነት ሲጠቅሱ ይታያል።


