Saturday, May 23, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ሊያካሂድ ነው።

የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ሊያካሂድ ነው።

ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!

የአማራ ክልል ምክር ቤት በመጪው ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም መደበኛ ጉባኤውን እንደሚያደርግ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል። ምክር ቤቱ ጉባኤውን የሚያደርገው በአማራ ሕዝብ ላይ የታወጀው ይፋዊ ጦርነት ሁለት ዓመታትን በሚደፍንበት ወቅት ላይ ነው።  

በአቶ አረጋ ከበደ የተተኩት የቀድሞው የክልሉ ርዕሰመስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በሐምሌ 27/2015 ዓ.ም የፌዴራል መንግሥቱ በክልሉ ጣልቃ እንዲገባ እና መከላከያ ሠራዊቱን ወደ አማራ ክልል እንዲያሰማራ በደብዳቤ ከጠየቁበት ጊዜ አንስቶ የአማራ ሕዝብ በጦርነት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ሁለት ዓመታትን ባስቆጠረው ጦርነት፣ በከባድ መሳሪያ እና በአየር ድብደባዎች እንዲሁም ቤት ለቤት በተፈፀሙ ግድያዎች በርካታ ንፁሐን ሕይወታቸውን፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ወድሟል፣ የኢኮኖሚ ጤና እና ማህበራዊ እንቅስቅሴዎች ተስተጓጉለዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የክልሉ ባለሥልጣናት “ፋኖን ሙሉ በሙሉ እስክናሸንፍ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል” የሚል አቋም መያዛቸውንና በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይም ይሄንኑ ያንፀባርቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

የክልሉ ባለስልጣናት ይሄንን ይበሉ እንጅ ባሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት የአማራ ፋኖ በተለያዩ የክልሉ ክፍለሀገራት በመከላከያ ሠራዊቱ እና በአድማ ብተና ኃይሉ ላይ ድል መቀናጀት መቻሉንና ከፍተኛ የጦር መሳሪያ በምርኮ ማግኘቱን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ።

የቀድሞው ርዕሰመስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ አማራ ክልል እንዲገባ ደብዳቤ መፃፋቸውን ተከትሎ፣ በቀድሞው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኃላፊ በአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሐምሌ 28/2015 ዓ.ም መታወጁ የሚታወስ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው የሚመሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ2016 ዓ.ም በጥር ወር መጨረሻ ላይ ድጋሚ ለአራት ወራት መራዘሙ አይዘነጋም። ከዚህ ጊዜ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መልሶ ባያራዝመውም፣ የአማራ ሕዝብ ዛሬም ድረስ አገልግሎት ላይ እየዋለ በሚገኝ እና በአራት ዕዞች በተዋቀረ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደገፈ ጦርነት እንደተከፈተበት የብዙዎች ዕምነት ነው።

በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ይደረጋል በተባለው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ፣ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት የተመለከተ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት እንደሚቀርብ የተነገረ ሲሆን፣ በክልሉ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚመሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለክልሉ ርዕሰመስተዳድር የተለያዩ መመሪያዎችን እንዳስተላለፉ ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ አቶ ተመስገን እና የክልሉን ርዕሰመስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ከሰሞኑ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፣ አገዛዙ ባሳለፍነው ሰኔ ወር በአማራ ክልል የጠራው ሰልፍ እንደ ማሳያ ተወስዶ የአማራ ሕዝብ የብልጽግናውን አገዛዝ እየደገፈ እንደሆነ አቶ አረጋ ለክልሉ ምክር ቤት ሪፖርት እንዲቀርቡ በአቶ ተመስገን ጥሩነህ መታዘዛቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።

የክልሉ የሕግ እንዲሁም የሠላምና ፀጥታ ሙያተኞች በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ጥናት ሰርተው ምክረ ሀሳባቸውን ለክልሉ ርዕሰመስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ማቅረባቸው የተነገረ ሲሆን፣ አቶ ተመስገን በበኩላቸው የሙያተኞቹ ምክረ ሀሳብ በምክር ቤቱ እንዳይቀርብ ጭምር ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ዞብል ፖስት ከምንጮቹ ሰምቷል።

የክልሉ ርዕሰመስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ ምክር ቤቱ በሚያካሂደው ጉባኤ ላይ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ የሚመለከት ሪፖርት በሚያቀርቡበት ወቅት፣ “መንግሥት ክልሉን ለመቆጣጠር እያደረገ ባለው ጥረት ጥሩ አፈፃፀም ማስመዝገቡንና ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን መቆሙን” ለምክር ቤቱ አባላት እንዲገልጹ ከአቶ ተመስገን ጥሩነህ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ “ፋኖን ሙሉ በሙሉ እስከናሸንፍ ድረስ ምክር ቤቱ የሕግ ማስከበር ዘመቻው እንዲቀጥል በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት” የሚል አቋም ሁለቱ ባለሥልጣናት ባደረጉት ውይይት ላይ መንፀባረቁን የመረጃ ምንጫችን አያይዘው ገልጸዋል።       

በመጪው ሐምሌ 19 ይካሄዳል በተባለው የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉ አመራሮች ላይ ሹም ሽር ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አያይዘው ገልጸዋል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች