Monday, May 18, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮች"የዘንድሮው ኢሬቻ የሚከበረው ለምርጫ 2018 መሠረት ለመጣል ነው!" የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ!

“የዘንድሮው ኢሬቻ የሚከበረው ለምርጫ 2018 መሠረት ለመጣል ነው!” የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ!

መስከረም 12/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!

የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል የሚከበርበት ዋነኛ ዓላማ ለመጪው 7ኛ ሀገራዊ እና ክልል አቀፍ ምርጫ 2018 መሠረት ለመጣል ነው መባሉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ያደረሱት መረጃ ያሳያል።

የዚህ ዓመት የኢሬቻ በዓል መስከረም 24 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በማግስቱ መስከረም 25 ቀን ደግሞ በደብረዘይት ከተማ ይከበራል ተብሎ ይጠበቃል።

የበዓሉን አከባበር በበላይነት የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ እና ደብረዘይት ከተሞች የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል የሚያስተባብሩ ተጠሪነታቸው ለዐቢይ ኮሚቴው የሆኑ ሌሎች ንዑስ ኮሚቴዎችም አብረው መዋቀራቸውን መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች ገልጸዋል።

እንደ ዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች የበዓሉን አከባበር እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው የተለያዩ ንዑስ ኮሚቴዎች በአዲስ አበባ፣ ደብረዘይት፣ እና ናዝሬት ከተሞች በኦሮሞ ብልጽግና መዋቅር ከተመለመሉ የበዓሉ ታዳሚዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም የግልና መንግሥት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በእነዚህ ከተሞች ላይ በተካሄዱ ውይይቶች ላይ የበዓሉ አስተባባሪዎች “የዘንድሮውን ኢሬቻ የምናከብረው ብልጽግና ፓርቲ በሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ አሸናፊ የሚሆንበትን መሠረት ለመጣል ነው” የሚል ሰነድ ለውይይት ማቅረባቸውን የመረጃ ምንጫችን ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል ተጠሪነቱ ለዐቢይ ኮሚቴው የሆነ ንዑስ ኮሚቴ በልደታ ክፍለ ከተማ የተቋቋመ ሲሆን፣ በመዲናዋ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጥብቅ ትዕዛዝ መተላለፉ ተነግሯል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በልደታ ክፍለ ከተማ የተቋቋመው ንዑስ ኮሚቴ ከከተማዋ ባለሀብቶች አስገዳጅ የሀብት ማሰባሰብ ስራ እየሰራ ሲሆን፣ የበዓሉ አጠቃላይ ወጪ ከከተማዋ ባለሀብቶች በሚሰበሰብ ገንዘብ ይሸፈናል መባሉን መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ እና ደብረዘይት ከተሞች የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል አከባበር የሚመራው ንዑስ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናትን እና የኦሮሞ ብልጽግና አመራሮችን ያካተተ ነው ተብሏል።

በተያያዘ ዜና፣ በዐቢይ አህመድ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ሲያነሱ የሚደመጡት በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኦሮሞ ልሂቃን በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ የበዓሉን ታዳሚዎች ለተቃውሞ ሊያነሳሱ ይችላሉ የሚል ስጋት በመንግሥት ዘንድ መኖሩን የመረጃ ምንጫችን አያይዘው ገልጸዋል።

ይሄንን ተከትሎ ሊከሰት ይችላል የተባለውን የፀጥታ ስጋት ለመከላከል በሚል ከፌዴራል እና ኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተውጣጣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል በአዲስ አበባ እና ደብረዘይት ከተሞች እንዲሰማራ ይደረጋል ተብሏል።  

የኢሬቻ በዓል “ሀይማኖታዊ ነው ወይስ ባህላዊ?” በሚል ያልተቋጨ ክርክር ሲካሄድበት የቆየ ሲሆን፣ ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ደግሞ በዓሉ ፖለቲካዊ አንድምታ እየያዘ መምጣቱን የተለያዩ ወገኖች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይስተዋላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ 2018 አሸናፊ የሚሆንበትን መሠረት ለመጣል ያለመ ነው መባሉን ተከትሎ፣ በመጪው መስከረም 24 እና 25 የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ድባብ ፖለቲካዊ ይዘቱ ጎልቶ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ኢትዮጵያ በጦርነት እና በሠላም እጦት እየታመሰችም ቢሆንም 7ኛውን ሀገራዊ እና ክልል አቀፍ ምርጫ አመች በሆኑ የሀገሪቷ አካባቢዎች እንደሚያካሂድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ አይዘነጋም።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች