Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮች"መከላከያ ሠራዊቱን ለሌላ ግዳጅ ልናዘጋጅ ስለሆነ የአማራ ክልልን ፀጥታ በራሳችሁ አቅም ለመቆጣጠር...

“መከላከያ ሠራዊቱን ለሌላ ግዳጅ ልናዘጋጅ ስለሆነ የአማራ ክልልን ፀጥታ በራሳችሁ አቅም ለመቆጣጠር መስራት አለባችሁ!” ጄኔራል አበባው ታደሠ!

መስከረም 14/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!

የመከላከያ ሠራዊቱ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ “መከላከያ ሠራዊቱን ለሌላ ግዳጅ ልናዘጋጅ ስለሆነ የአማራ ክልልን ፀጥታ በራሳችሁ አቅም ለመቆጣጠር መስራት አለባችሁ” ሲሉ ከአማራ ክልል ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት መናገራቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።

ጄኔራሉ የአማራ ክልል መንግሥት ክልሉን ከመከላከያ ሠራዊቱ ተረክቦ ለማስተዳደር መንቀሳቀስ እንዳለበት ከክልልና ዞን ባለሥልጣናት ጋር እያደረጉት ባለው ውይይት ማሳሰባቸውን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ምክትል ኢታማዦር ሹሙ በቅድሚያ በደብረ ብርሃን ከተማ ቀጥሎም በኮምቦልቻ ተገኝተው ከክልልና ዞን ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ በመጪዎቹ ቀናት ደግሞ በጎንደር እና ባህርዳር ከተሞች ተመሳሳይ ውይይቶችን ያደርጋሉ መባሉን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

እንደ ዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች ምክትል ኢታማዦር ሹሙ መከላከያ ሠራዊቱን ለሌላ ግዳጅ የማዘጋጀት እቅድ አለን በማለት የአማራ ክልል መንግሥት የራሱን የፀጥታ መዋቅር በማጠናከር ክልሉን ከመከላከያ ለመረከብ መስራት እንዳለባቸው ለተሰብሳቢ ባሥልጣናቱ አስረድተዋል ተብሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከሰሞኑ ለተለያዩ ወታደራዊ አመራሮች የማዕረግ እድገት መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ለወታደራዊ አመራሮቹ የተሰጠው የማዕረግ እድገት አንድምታ ከጄኔራል አበባው “መከላከያ ሠራዊቱን ለሌላ ግዳጅ ልናዘጋጅ ነው” ከሚለው ንግግር ጋር የሚያያዝ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ርዕሰመስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ ለመገምገም በተሰበሰበበት ወቅት፣ “ክልሉን ከመከላከያ ሠራዊቱ ለመረከብ አቅማችንን ማጠናከር አለብን” ማለታቸውን ባሳለፍነው ሳምንት መዘገባችን አይዘነጋም።

ይሄንን ታሳቢ በማድረግም የአማራ ክልል መንግሥት በጀቱን ሙሉ በሙሉ ለሚሊሻ እና የአድማ ብተና ምልመላ እና ስልጠና ተግባራት እያዋለው እንደሚገኝ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ምክትል ኢታማዦር ሹሙ እና የክልሉ ርዕሰመስተዳድር ይሄንን ይበሉ እንጅ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ከአማራ ፋኖ ጋር እያደረገ ባለው ጦርነት ተከታታይ ሽንፈቶችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ከአማራ ክልል የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ጄኔራል አበባው ታደሠ መከላከያ ሠራዊቱን ለሌላ ግዳጅ ስለማዘጋጀት ያነሱትን እቅድ በዝርዝር ባያስረዱም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ ከመጣው የሁለቱ ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች