መስከረም 15/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ የፅሁፍ አቤቱታ ማቅረቡን ድርጅቱ በዛሬው ዕለት አስታውቋል።
በዋና ሰብሳቢው እስክንድር ነጋ የሚመራው አፋሕድ ለጠቅላላ ጉባኤው በላከው አቤቱታ፣ የአማራ ሕዝብ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ከፍተኛ የሆነ የጀምላ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ የሃብትና ንብረት ቃጠሎ፣ የኃይማኖት ተቋማት ውድመት ሲደርስበት ኖሯል፣ አሁንም እየደረሰበት ይገኛል ያለ ሲሆን፣ የዓለም ሀገራት ይሄንን ሁኔታ አፅንኦት እንዲሰጡት ጠይቋል።
ድርጅቱ አቤቱታውን ባቀረበበት ደብዳቤ ላይ ዓለም በዝምታ እየተመለከተው ያለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተራ ግጭትና የፀጥታ አለመረጋጋት አለመሆኑን በመጠቆም፣ በኢትዮጵያ ስር የሰደደ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተካሄደ ይገኛል ሲል ገልጿል።
እንደ ድርጅቱ አቤቱታ፣ በተለየ ሁኔታ ባለፉት ሰባት ዓመታት፣ ማለትም ዐቢይ አህመድ የሀገር መሪነቱን ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል በጣም አስከፊ ሆኗል ሲል አብራርቷል።
በዐቢይ አህመድ መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች፣ እንዲሁም፣ የታጠቁ ሚሊሻዎች የአማራ ሕዝብን በከፊል ወይም በሙሉ ለማጥፋት አስበው እና አቅደው የጥቃት ዒላማ አድርገውታል ያለው አፋሕድ፣ እነዚህ ድርጊቶች እ.ኤ.አ. በ1948 (በተባበሩት መንግሥታት) የወጣውን የዘር ማጥፋት ስምምነት እና በሮም ስምምነት አንቀጽ ስድስት ስለ ዘር ማጥፋት የወጡትን መሥፈርቶች ያሟላሉ ብሏል።
አፋሕድ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባኤ የመጣነው በኢትዮጵያ ባለው የፍትህ ስርዓት መፍትሄ ማግኘት ባለመቻላችን ያለ ሲሆን በተቃራኒው፣ የፍትህ ሥርዓቱ የወንጀሉ አካል ሆኗል በማለት በአቤቱታው ገልጿል።
አፋሕድ የአማራ ሕዝብ ሀገራዊ የሕግ ከለላ በሌለው እንደሚገኝ በማሳሰብ፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ እያሳየ ያለው ዝምታ ወንጀለኞችን የሚያበረታታ እንጂ መፍትሄ የሚያመጣ አለመሆኑን በአቤቱታው አስረድቷል።
ድርጅቱ የተባበሩት መንግሥትታት ጠቅላላ ጉባኤ በትኩረት እንዲመለከታቸው የተለያዩ አንኳር ነጥቦችን በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ከእነዚህም መካከል፤
በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል እውቅና ሰጥቶ እንዲያወግዝ፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት አስፈፃሚነት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በገለልተኛ ምርመራ ቡድን እንዲጣራ እንዲያደርግ በአቤቱታ ጠይቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ላወጣው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ገለልተኛ ማጣራት እንዲያደርግ መጠየቁ አይዘነጋም።
ከዚህም በተጨማሪ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ወንጀለኛ ባለስልጣናት ወደ ሕግ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ፣ እና በሕዝብ ላይ የባሰ ጭፍጨፋ እና መፈናቀል እንዳይከሰት አፋጣኝ እርምጃ በአስቸኳይ እንዲወስድ እንጠይቃለን ሲል አፋሕድ ለጠቅላላ ጉባኤው በላከው አቤቱታ ጠይቋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም የዓለም መንግሥታት “ከዚህ በኋላ የዘር ማጥፋት ወንጀል አይደገምም” ብለው ቃል ኪዳን ማሰራቸውን በማስታወስ፣ ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማራዎችን ህልውና እና የአፍሪካ ቀንድን ሰላም በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጠይቋል።


