መስከረም 26/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ቢልኤ አህመድ “አሰብን የአፋር ክልል ሰባተኛ ዞን እናደርጋታለን” ማለታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ያደረሱት መረጃ ያሳያል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ይሄንን የተናገሩት ከሰሞኑ ከአፋር ክልል፣ ዞኖች እና ወረዳዎች ከተውጣጡ የፖሊስ አመራሮች፣ አባላት እና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ነው ተብሏል።
አፋር ክልል አዲስ የተቋቋመውን ማሂ ረሱ ዞንን ጨምሮ አውሲ ረሱ፣ ክልበቲ ረሱ፣ ጋቢ ረሱ፣ ፋንቲ ረሱ፣ እና ሀሪ ረሱ ተብለው የሚጠሩ ስድስት ዞኖች ያሉት ሲሆን፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቢልኤ አህመድ ሰባተኛውን ዞን አሰብ ላይ እናቋቁማለን ማለታቸውን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
እንደ ዞብል ፖስት የመረጃ ምንጭ አሰብን የአፋር ክልል ሰባተኛው ዞን እናደርጋታለን ያሉት ፖሊስ ኮሚሽነሩ አሰብን ለማስተዳደር እና ለተያያዥ የፀጥታ ጉዳዮች ዝግጅት ማድረግ አለብን ሲሉ ለክልሉ ፖሊስ አመራሮች፣ አባላት፣ እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት መልዕክት አስተላልፈዋል ተብሏል።
ኮሚሽነሩ ይሄንን ይበሉ እንጅ የአፋር ክልል ፖሊስ አባላት በኤርትራ የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኙ የአፋር ተቃዋሚ ኃይሎችን በመቀላቀል ላይ እንደሚገኙ በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተያያዘ ዜና የቀይ ባሕርን አጀንዳን ከዞንና ወረዳ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የፀጥታ አካላት ጋር ውይይት እንዲያደርጉበት ከፌዴራል መንግሥቱ ለክልሎች ትዕዛዝ መውረዱ ተነግሯል።
የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቢልኤ አህመድም አሰብን የአፋር ክልል ሰባተኛ ዞን እናደርጋታለን ያሉት የቀይ ባሕርን ጉዳይ አጀንዳ እንዲያደርጉ ከፌደራል መንግሥቱ የወረደውን ትዕዛዝ ተከትሎ መሆኑን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።


