Saturday, May 23, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችበሻሸመኔ ከተማ የሚኖሩ ራስ ተፈሪያውያን ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ ጫና እየተደረገባቸው ነው።

በሻሸመኔ ከተማ የሚኖሩ ራስ ተፈሪያውያን ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ ጫና እየተደረገባቸው ነው።

ጥር 16/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!

በሻሸመኔ ከተማ የሚኖሩ የራስ ተፈሪያውያን ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን ዞብል ፖስት ከከተማዋ ነዋሪዎች ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ራስ ተፈሪያውያኑ ጫና እየተደረገባቸው ያለው ከኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ኃይሎች ሲሆን “የክልሉን ገፅታ እያበላሻችሁ ነው” በሚል የሻሸመኔ ከተማን ለቅቀው እንዲወጡ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ጫናዎች እየደረሱባቸው እንደሚገኝ መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

በከተማዋ የሚገኙ ራስ ተፈሪያውያን “የንጉሳውያን ስርዓትን ታመልካላችሁ” በሚል ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ ወይንም በጉዲፈቻ አማካኝነት የገዳ ስርዓት አምልኮን እንዲቀበሉ ጫና ከመፍጠር ጀምሮ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ የአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ አላማን እንዳይይዙ ክልከላ እየደረሰባቸው ይገኛል።

የተጠየቁትን ለማድረግ ያልቻሉ እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ እንዲከፍሉ በፀጥታ ኃይሎች እንደሚጠየቁም መረጃውን ያደረሱን ምንጮች አያይዘው ጠቅሰዋል።

ይሄንን ተከትሎ ለበርካታ ዓመታት ከኖሩባት ሻሸመኔ ከተማ ለቅቀው እየወጡ እና ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ወደተለያዩ ሀገራት እየተበተኑ እንደሚገኙ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያመላክታል።

ራስ ተፈሪያውያን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ምልክቶች ያሉባቸውን አልባሳት እና ቁሳቁስ ይዘው መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ከማድረግ ጀምሮ ለበርካታ አሥርት ዓመታት ጠብቀው ያቆዩዋቸውን እሴቶች እንዳያንፀባርቁ ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ተነግሯል።

ራስ ተፈሪያውያኑ እየደረሰባቸው ያለውን ጫና ተከትሎ ለሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር እና ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ተደጋጋሚ አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ “ወደዚህ ያመጧችሁን አፄ ኃይለሥላሴን ጠይቁ” የሚል የሹፈት ምላሽ እንደሚሰጣቸው መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አክለው አስረድተዋል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች