Friday, May 8, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየኢትዮጵያ መንግሥት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱን እና ለፕሮጀክቱ ሲባል ዜጎችን በግዳጅ ማፈናቀሉን እንዲያቆም...

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱን እና ለፕሮጀክቱ ሲባል ዜጎችን በግዳጅ ማፈናቀሉን እንዲያቆም አምነስቲ ኢንተርናሽናልአሳሰበ።

ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል አዲስአበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተካሄደ በሚገኘው የኮሪደር ልማት፣ ከዜጎች ጋር ተገቢ ምክክር ሳይደረግ እና አስፈላጊው የካሳ ክፍያ ሳይፈፀም “ዜጎችን ከቤታቸው በግዳጅ የማፈናቀል” ተግባር እየተፈፀመ መሆኑን በመግለፅ የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳሰበ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሚያዚያ 6፣ 2017 ዓ.ም ባወጣው የጥናት ሪፖርት፣ ከቦሌ እና ለሚኩራ ክፍለከተሞች ብቻ 872 ያህል ዜጎች ለኮሪደር ልማት በሚል አስገዳጅ በሆነ መንገድ በመንግሥት እንደተፈናቀሉ አብራርቷል። ከተፈናቃዮቹ መካከል 254 የሚሆኑት የቤት ባለቤቶች ሲሆኑ 618 የሚሆኑት ደግሞ ተከራዮች ናቸው ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ እንደገለፀው፣ መንግሥት በግዳጅ የማፈናቀል ተግባርን እየፈፀመ ያለው ለዜጎች ህጋዊ እና ሌሎች ጥበቃዎችን ሳያደርግ ነው። ይህ በግዳጅ ማፈናቀል “ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ” ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ላይ አስረድቷል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርቱን ለማዘጋጀት ከቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለከተሞች 55 የሚሆኑ በኮሪደር ልማት ስም ቤታቸው የፈረሰባቸውንና የግዳጅ መፈናቀል የተፈፀመባቸውን ሰዎች አነጋግሯል። ከዚህም በተጨማሪ፤ የሳተላይት ምስል ምልከታ ማድረጉንና በትንሹ 29 ሄክታር ገደማ የሚሆን አካባቢ መፍረሱን ሪፖርቱ አያይዞ ያስረዳል። 

ሪፖርቱ አክሎም፣ የኮሪደር ልማቱ ለዜጎች የእለት ተለት ግንኙነትና ትብብር መሠረት የሆኑ እንደ እድር ያሉ ማህበረሰባዊ ተቋማት እንዲበተኑ በማድረጉ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ የማህበራዊ ግንኙነቶች ሊቋረጡ መቻላቸውን ነዋሪዎችን ጠቅሶ አስረድቷል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የግዳጅ መፈናቀል ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ቃለምልልስ አድርጎ “ብዙዎች ስነልቦናዊ ቀውስ እና የአዕምሮ ጤና ችግር አጋጥሟቸዋል” ሲል በጥናቱ አመላክቷል። ከዚህ በተጨማሪ የህፃናት ትምህርት መስተጓጎሉን አምነስቲ ገልጿል።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ለልማት ፕሮጀክቶች ዜጎችን ማፈናቀል የመጨረሻ አማራጭ ሊሆን የሚገባው ውሳኔ መሆኑን ጠቅሶ፣ ይሄም የዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ ሁኔታ ሊተገበር ሲገባው “የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በግዴለሽነት እና የዜጎችን ዕጣፋንታ ከግምት ውስጥ ባላስገባ ሁኔታ የግዳጅ መፈናቀል ተግባር ፈፅሟል” ሲል በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ወቀሳ አቅርቧል።

የዜጎችን መኖሪያ ቤት በማፍረስ ሂደት ውስጥ፤ ከዜጎች ጋር አስፈላጊውን ምክክር ባለማድረግ፣ ተገቢውን የአሰራር ሂደት ባለመከተል፣ እና ቤታቸው ለሚፈርስባቸው ዜጎች በተተኪ የቤት አቅርቦት ለመካስ ባለመቻል መንግሥት “በእነዚህ ሶስት መንገዶች የዜጎችን የሰብዓዊ መብት ላይ ጥሰት ፈፅሟል” ብሏል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች