Friday, May 8, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ በሶማሌው ጋዜጠኛ ላይ የተላለፈው የሁለት ዓመት እስራት...

ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ በሶማሌው ጋዜጠኛ ላይ የተላለፈው የሁለት ዓመት እስራት “አሳዝኖኛል” ሲል ገለፀ።

ሲፒጄ የጅግጅጋ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ጋዜጠኛ የሆነው አህመድ አውጋ፣ “ባላስተላለፈው የፌስቡክ መልዕክት ምክንያት የሁለት ዓመት እስራት ሊፈረድበት መቻሉ አሳዛኝ ውሳኔ ነው” በማለት ገልጻል። ጋዜጠኛው፣ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ በግንቦት 14፣ 2017 ዓ.ም የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።  

ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ አህመድ አውጋ በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋ በሚገኘው የፋፈን ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለው፣ በ2012 ዓ.ም የወጣውን የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት አዋጅ ተላልፏል በሚል ወንጀል መሆኑን አስታውቋል።

ጋዜጠኛ አህመድ አውጋ “በተፈፀመበት የፖሊስ ድብደባ ምክንያት ህይወቱ ካለፈ ግለሰብ አባት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንዲሁም ጉዳዩን ተከትሎ ሌሎች ሰዎች በፌስቡክ ገጾች ላይ በሰጡት አስተያየት ምክንያት ከሚያዚያ 15፣ 2017 ዓ.ም አንስቶ በእስር ላይ ቆይቷል” ሲል ሲፒጄ ጉዳዩ እንዳሳዘነው በገለፀበት መግለጫ አስነብቧል።

ጋዜጠኛ አህመድ አውጋ፣ መጀመሪያ ላይ የወንጀል ድርጊቶችን በመቀስቀስ ተከሶ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ሲፒጄ በተመለከተው የክስ መዝገብ ላይ ክሱ “ሀሰትኛ መረጃዎችን ማሰራጨት እና ህዝብን ማነሳሳት” ወደሚል መቀየሩ አመላክቷል።

አህመድ አውጋ “የክልሉን ምርጫ ሀሰተኛ ምርጫ ነው፣ የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ህዝቡን በግዞት ይዘው እያስጨነቁ ነው፣ የሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ተይዘዋል፣ ህዝብን ለማነሳሳት በክልሉ ግድያ እና ሞት እንጂ ፍትሕ የለም” የሚሉ ሃሳቦችን በሚያዝያ 9፣ 2017 ዓ.ም በፌስቡክ ትስስር ገፁ ላይ አስፍሯል የሚል ክስ እንደቀረበበት የጋዜጠኛውን የክስ መዝገብ ጠቅሶ ሲፒጄ ገልጿልል።

ጋዜጠኛ አህመድ ጥፋተኛ የተባለው በሚያዝያ 12፣ 2017 ዓ.ም በፌስቡክ ገፅ በተለጠፈ ፅሁፍ ላይ በተመሰረተ ክስ ሲሆን፣ ልጥፉ የሚገኘው “በተከሳሹ አህመድ ገፅ ላይ ሳይሆን ጋዜጠኛ አህመድ ታግ በተደረገበት በሌላ ግለሰብ በሚተዳደር የፌስቡክ ገፅ ነው” በማለት ሲፒጄ አያይዞ ገልጿል።

በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ ሶማሊ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሐመድ በበኩላቸው፣ “ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ገፆች በሚያስተላለፉት መልዕክት ብቻ አይታሰሩም” በማለት ሲፒጄ ያቀረበውን ቅሬታ ውድቅ አድርገዋል።

ሙስጠፌ አያይዘው፣ “አንድ ጋዜጠኛ፣ አንድ የቀድሞ ባለሥልጣን፣ እና ሁለት የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የክልሉን የፀጥታ አካላት ስም በማጥፋት እና የእስረኞችን መረጃ በሀሰተኛ መንገድ በማሰራጨት ተጠርጥረው ታስረዋል” በማለት ገልፀዋል።

ሲፒጄ  በበኩሉ፣ በአህመድ ላይ የተላለፈው ቅጣት “ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ላይ የምታደርሰው አፈና መጨመሩን የሚያሳይ እና ባለሥልጣናት የተቃውሞ ድምጾችን ለማፈን የሕግ ስርዓቱን እንደ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑን የሚያሳየ ነው” በማለት በጋዜጠኛው ላይ የተላለፈውን የፍርድ ቤት ውሳኔ አሳዝኝ ሲል ገልጾታል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች