የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ከሰሞኑ ባልተለመደ መልኩ በመደበኛ ስራቸው ላይ እየተገኙ አለመሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
ፊልድ ማርሻሉ፣ በመደበኛ የስራ ገበታቸው ላይ እየተገኙ ያልሆነው ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፣ ከዚህ ቀደም የአተነፋፈስ የጤና ችግር እንደነበረባቸው የጠቆሙት የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች፣ ይሄው የጤና እክል ከሰሞኑ መልሶ ሳያገረሽባቸው እንዳልቀረ አያይዘው አስረድተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከአየር ኃይል አዛዡ ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ጋር፣ ባሳለፍነው ሳምንት የጦር መሳሪያ ግዥ ለመፈፀም ከሄዱበት ራሺያ ወደ ሀገር ቤት መመለሳችው ይታወሳል። ኢታማዦር ሹሙ ከራሺያ ከተመለሱ በኋላ በመደበኛ የስራ ገበታቸው ላይ በተደጋጋሚ ቀናት አልተገኙም።
ፊልድ ማርሻሉ ወደ ቢሮ ካለመግባትም በተጨማሪ፣ ከራሺያ ጉዟቸው መልስ በተደረገው የወታደራዊ ካውንስሉ ስብሰባ ላይም ሊገኙ እንዳልቻሉ፣ መረጃውን ለዞብሎ ፖስት ያደረሱት ምንጮች አያይዘው አስረድተዋል።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ በስራ ገበታቸው ላይ ለመገኘት አለመቻላቸውን ተከትሎ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ የወታደራዊ ደህንነት ኃላፊ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የፊልድ ማርሻል ብርሃኑን ቦታ በጊዜያዊነት ተክተው ለሠራዊቱ አመራር እየሰጡ እንደሚገኙ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ “ጠቅላይ ኢታማዦሩ በስራ ገበታቸው ላይ ሳይገኙ ሲቀሩ፣ እሳቸውን በጊዚያዊነት ተክቶ ሊሰራ የሚገባው ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል አበባው ታደሠ አይደለም ወይ?” የሚል ጥያቄ ለመረጃ ምንጫችን ያቀረብን ቢሆንም፣ የመረጃ ምንጫችን ባቀረብንላቸው ጥያቄ ዙሪያ በቂ መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል።


