ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ከፍተኛ መከፋፈል ምክንያት፣ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የቀድሞ የህወሓት አባላት፣ ከህወሓት በመውጣት “ዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ” የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት መመስረታቸው የተሰማው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።
ዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ ፓርቲ፣ የመጀመሪያውን ጋዜጣዊ መግለጫ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል የሰጠ ሲሆን፤ በመግለጫው ወቅት “የህወሓት አባል ሁኖ ለውጥ የሚፈልግ አካል ካለ የፓርቲያችን አባል መሆን ይችላል” ሲል አዲሱ የትግራይ ፓርቲ “የተቀላቀሉን ጥሪ” አቅርቧል፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ በህመም ምክንያት በመግለጫው ላይ መገኘት ባለመቻላቸው ምክንያት፣ መግለጫውን የሰጡት የፓርቲው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ እና የአደራጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ረዳዒ ሐለፎም ናቸው። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፓርቲው መስራቾች የሚገኙት በትግራይ እንደሆነም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ጠቁመዋል፡፡
አዲሱ ፓርቲ፣ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት በትግራይ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚያካሄድ የተሰማ ሲሆን፣ መስራች አባላቶቹ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ከክልል እስከ ቀበሌ አደረጃጀቶችን የመመስረት እና አባላትን የመመልመል ሥራዎችን ለማከናወን ወደ ትግራይ ክልል ጉዞ እንደሚያደርጉ ተሰምቷል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ “ዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ” በክልሉ የአደረጃጀት እና የአባላት ምልመላ ስራን ለማከናወን እቅድ መያዙን ተከትሎ፣ በህወሓት በኩል ትንኮሳዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ በሚል ስጋት፣ በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት ጥበቃ ለማድረግ ቅድመ-ስምሪት ሊሰጣቸው እንደሚችል ይገመታል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው አዲሱ ፓርቲ፣ የትግራይ ግዛታዊ አንድነትን ማስከበር የሚል አቋም በህገ ደንቡ ያስቀመጠ ሲሆን፣ የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ የማንነት እና ርስት ጥያቄዎች የሚያነሳባቸውን እንደ ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት፣ ራያ እና አበርገሌ ያሉ አካባቢዎችን የትግራይ አካል አድርጎ የሚቆጥር ስለመሆኑም ታውቋል፡፡


