በደብረብርሃን ከተማ በሶስት የተለያዩ የተፈናቃይ ጣቢያዎች ከ24 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፣ የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት USAID የሚያደርግላቸው ድጋፍ በመቋረጡ ምክንያት ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ገልፀዋል።
ተፈናቃዮቹ፣ ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ፣ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በመንግሥት እና በኢ-መደበኛ ታጣቂዎች በማንነታቸው ምክንያት ከሚፈፀምባቸው ግድያ ሸሽተው፣ እንዲሁም በሸገር ከተማ ቤታቸው ፈርሶባቸው ወደ አማራ ክልል የተፈናቀሉ ናቸው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈው ስልጣን በያዙ ማግስት፣ የUSAID በጀት እንዲታጠፍ እና ድርጅቱ ለተለያዩ ሀገራት የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቋረጥ መወሰናቸው ይታወሳል። ውሳኔው ለተረጅዎች በሚቀርብ የምግብ ስርጭት፣ የጤና እንክብካቤ፣ እና የተፈናቃዮች ድጋፍ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው።
በዚህ ምክንያት፣ ከዚህ ቀደም በደብረብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከተራድኦ ድርጅቱ ይደረግ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ መቆሙን እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ አደጋ መጋለጣቸውን፣ ዞብል ፖስት በደብረብርሃን ከሚገኙ የተፈናቃይ ጣቢያዎች ያገኘው መረጃ ያመላክታል።
በከተማዋ ሶስት የተፈናቃይ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በባቄሎ ጣቢያ ከ5,400 በላይ፣ በወይንሸት ጣቢያ ከ6,800 በላይ፣ እንዲሁም በቻይና ጣቢያ ከ12,000 የሚበልጡ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ፣ ዞብል ፖስት በተፈናቃይ ጣቢያዎቹ በሰብዓዊ አገልግሎት ላይ ከተሰማሩ በጎ ፈቃደኞች ያገኘው መረጃ ያሳያል።
ተፈናቃዮቹ ከገጠሟቸው ዋና ዋና ችግሮች መካከል በቂ እና መደበኛ የምግብ አቅርቦት አለመኖር አንዱ ነው። ችግሩ እንዳጋጠመ ቢታወቅም፣ “ከመንግሥት አካላት በቂ ክትትልና ድጋፍ ማግኘት አልቻልንም” ሲሉ ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች አስረድተዋል።
ሌላኛው እጅግ አሳሳቢ ችግር፣ ለህፃናት የሚያስፈልገው የአልሚ ምግብ እጥረት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። በሶስቱ የተፈናቃይ ጣቢያዎች በጥቅሉ፣ እድሜያቸው ከአንድ እስከ አምስት የሆኑ ከ3,000 በላይ ህፃናት የሚገኙ ሲሆን፣ ለህፃናት የሚያስፈልጉ የአልሚ ምግቦችን በአግባቡ ማግኘት አለመቻላቸውን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በደብረብርሃን ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ፣ ህፃናትን ጨምሮ ወደ 13,000 የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያሳያል። በእነዚህ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሴቶች እና እናቶች፣ የንፅህና እና ፅዳት መጠበቂያ ቁሳቁስ እና ግብዓት እጥረቶች እንደገጠሟቸው ለማወቅ ተችሏል።
የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ዞብል ፖስት ከዚህ ቀደም ከሌሎች ወገኖች ይቀርብላቸው የነበሩ ድጋፎችን በተመለከተ ተፈናቃዮችን አነጋገሮ የነበረ ሲሆን፣ “ከሀገር ውስጥም ከውጭም እርዳታ እናሰበስባችኋለን የሚሉ አካላት አሉ፣ የሚደርሰን ድጋፍ ግን በሚዲያዎች የሚነገረውን ያህል አይደለም” በማለት አስረድተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ውስጥ ለተረጂዎች የሚያቀርበውን ዕርዳታ ለመቀነስ አስገዳጅ ሁኔታዎች እንደገጠሙት፣ ድርጅቱ ከሰሞኑ አሳውቋል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ከተለያዩ ለጋስ ድርጅቶች እርዳታን ለሚጠባበቁ በደብረብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል።


