Friday, October 23, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዘገባዎችአራት ኪሎአቶ ታየ ደንደዓ ከሀገር ሊሰደዱ ይችላሉ ተብለው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

አቶ ታየ ደንደዓ ከሀገር ሊሰደዱ ይችላሉ ተብለው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

አቶ ታየ ደንደዓ ከዚህ ቀደም ነፃ ተብለው የነበሩባቸው ሁለት ክሶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በድጋሜ እንዲቀጥሉ መወሰኑን ተከትሎ፣ ዛሬ ከከሰዓት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል።

ጉዳዩን ተከትሎ ዞብል ፖስት ባደረገው ተጨማሪ ማጣራት፣ መንግሥት አቶ ታየ ደንደዓ ከሀገር ሊወጡ ይችላሉ የሚል መረጃ እንደደረሰውና በቀድሞ አለቃቸው ዐቢይ አህመድ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ዛሬ አመሻሹን መታሰራቸው የደረሰን መረጃ ያሳያል።

ከዚህ ቀደም የዐቢይ አህመድን አገዛዝ “በሀገር ህልውና ስም ኢትዮጵያውያንን የሚያገዳድል እና ሀገሪቷን እያደቀቀ ያለ ጦርነት እያካሄደ ነው” ዐቢይ አህመድንም “በሰዉ ደም የሚጫወት አረመኔ ግለሰብ” በማለታቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገው እንደነበር የሚታወስ ነው።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ እና የኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) አባል የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ፣ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከሹመታቸው ተነስተው በሶስት ክሶች ተጠርጥረው ረዘም ላለ ጊዜ ታስረው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ዛሬ ከከሰዓት በድጋሚ መታሰራቸው ተሰምቷል።

አቶ ታዬ ከዚህ ቀደም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ነፃ የተባሉት፣ “ከጠላት ጋር በመተባበር” እና “የፀረ-ሰላም ቡድኖች የሆኑትን ሸኔ እና ፋኖን የሚደግፉ መልዕክቶችን በፌስቡክ ገፃቸው አጋርተዋል” በሚሉት ክሶች ሲሆን፣ አቃቤ ሕግ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱን ተከትሎ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመሻር መዝገቡን መልሶታል።

የቀደሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ነፃ ተብለው፣ የጦር መሳሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ ቀርቦባቸው የነበረው ሶስተኛው ክስ ግን ከእስር ተለቀው በውጭ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷቸው ከህዳር 26፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከእስር ቤት ወጥተው ጉዳያቸውን በውጭ ሲከታተሉ እንደነበር ይታወሳል።

አቃቤ ህግ አቶ ታየ ከተመሰረተባቸው ሁለቱ ክሶች ነፃ መባል የለባቸውም የሚል ይግባኝ ማስገባቱን ተከትሎ፣ ጉዳያቸው ዳግም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መታየት አለበት በሚል በድጋሚ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

ይሁን እንጅ፣ አቶ ታየ ደንደዓ ከሀገር ለመውጣት እና በመንግሥት ላይ ሠላማዊ ትግል ለማቀጣጠል እንቅስቃሴ ጀምረዋል የሚል መረጃ ለመንግሥት መድረሱን ተከትሎ፣ “የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲያውሏቸው ለማድረግ፣ ሁለቱ ክሶች ከእንደገና እንዲታዩ ተወስኗል” ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል። 

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች