በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ አካባቢ ወርቅ ለማውጣት ወደ ኢትዮጵያ የመጣ አንድ የግብፅ ኩባንያ፣ ፈቃድ ካወጣበት የማዕድን ዘርፍ ውጭ የመረጃና ደህንነት ሥራ ላይ ተሰማርቷል ተብሏል።
መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች እንደገለጹት፣ በዚሁ ተግባር ላይ የተሰማራው ድርጅት ግብፃውያን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት “አስኮም ኢንተርናሽናል” የተባለው የወርቅ ማዕድን አውጪ ኩባንያ ነው።
ምንጮቹ አክለውም፣ “የኩባንያው ዋነኛ ትኩረት የማዕድን ሀብት ማፈላለግ ሳይሆን የመረጃ ሀብት መሰብሰብ” መሆኑን አስታውቀዋል።
የመረጃ ምንጮቻችን እንደገለጹት፣ አስኮም ኢንተርናሽናል የተባለው ኩባንያ የግብፅ የመረጃና ደህንነት ሰዎችን በአባይ ተፋሰስ ቀጠና ለመረጃና ደህንነት ሥራ አሰማርቷል። እነዚህ ግብፃውያን የመረጃና ደህንነት ሰዎች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ማንኩሽ” ከሚባለው አካባቢ ተነስተው እስከ ቻግኒ ድረስ በተደጋጋሚ ቅኝት ያደርጋሉ።
የወርቅ አውጪ ኩባንያ ተብሎ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ የተሰማራው ይኸው ኩባንያ፣ የውሃ መሃንዲሶችንና ሰላዮችን በሠራተኝነት ቀጥሮ በአባይ ወንዝ ዙሪያ እና በጣና ሃይቅ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ቅኝቶችን ያደርጋል።
ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው፣ እነዚህ የውሃ መሃንዲሶች የአባይ ምንጮች ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ አካባቢዎችንና ገባር ወንዞችን ተዟዙረው የማየትና መረጃ የመሰብሰብ ሥራ ያከናውናሉ።
ለኩባንያው የመረጃና ደህንነት ሥራ የመተከል ዞንና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሥልጣናት ተባባሪ እንደሆኑ፣ የአስኮም ኢንተርናሽናል የቴክኒክ ረዳቶችንና አሽከርካሪዎችን በቅርበት የሚያውቃቸው የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጭ ገልጿል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ሀገርን ከውስጥና ከውጭ ሊቃጡ ከሚችሉ ስጋቶች መረጃን ቀድሞ የማግኘት ኃላፊነት ያለበት ሬድዋን ሁሴን የሚመራው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት (NISS)፣ በጉዳዩ ላይ መረጃ ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር የለም።


