ሰኔ 20/2017–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
ህወሓት የትጥቅ ትግል ለመጀመር በቅርቡ ወደ ትግራይ ክልል ለገቡ የአፋር ታጣቂዎች በክልሉ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ያደረሱት መረጃ ያሳያል።
ወደ ትግራይ ክልል ተጉዘው በህወሓት ወታደራዊ አመራሮች ወታደራዊ ስልጠና የጀመሩት የአፋር ታጣቂዎች ስልጠና የጀመሩት ምስራቃዊ ዞን ተብሎ በሚጠራው የትግራይ ክልል መሆኑን ምንጫችን አክለው ገልፀዋል።
ምስራቃዊ ዞን ተብሎ የሚጠራው ይህ የትግራይ ክልል አካባቢ ትግራይን ከአፋር ክልል ጋር የሚያዋስን ሲሆን፣ በህወሓት ስልጠና የሚሰጣቸው የአፋር ታጣቂዎች በቦታው ወታደራዊ ሰፈር ማቋቋማቸውን ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከስልጣን ተነስተው በአወል አርባ የተተኩት እና መቀመጫቸውን በመቀሌ አድርገው የነበሩት የቀድሞው የአፋር ክልል ርዕሰመስተዳድር ሐጅ ስዩም፣ በትግራይ ክልል የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ከጀመሩት የአፋር ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው እንደማይቀር ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያመላክታል።
የመረጃ ምንጫችን አክለውም፣ ከዚህ ቀደም የሐጅ ስዩም ጎሳዎች ከወቅቱ የአፋር ክልል ርዕሰመስተዳድር አወል አርባ ጎሳዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር በማስታወስ፣ በትግራይ ክልል በህወሓት ወታደራዊ ስልጠና እየተሰጣቸው የሚገኙት የአፋር ታጣቂዎች ከሐጅ ስዩም ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው አይቀርም መባሉ ከዚህ በፊት በአፋር ክልል ተከስቶ የነበረው አይነት የጎሳ ግጭት መልሶ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐጂ ኢብራሒም ዑስማን የሚመሩት የአፋር ታጣቂ ቡድን በቅርቡ በኤርትራ የትጥቅ ትግል መጀመሩን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ። ቡድኑ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ስልጠና ከጀመረው ሌላኛው የአፋር ታጣቂ ኃይል ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ግን የታወቀ ነገር የለም።
በሌላ በኩል በአቶ ጌታቸው ረዳ ይደገፋል የሚባለው እና በብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ የሚመራው ከህወሓት የወጡ ወታደራዊ መሪዎች እና ታጣቂዎች ያቋቋሙት የትግራይ ታጣቂ ቡድን በቅርቡ በአፋር ክልል መጋሊ ቀጠና ወታደራዊ ስልጠና ጀምሯል።
ይሄንን ተከትሎ ህወሓት በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን የአፋር ታጣቂዎችን ማሰልጠን የጀመረው በአፋር ክልል የትጥቅ ትግል ለጀመረው የእነ ገብረእግዚአብሔር በየነ የትግራይ ታጣቂ ቡድን አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ የመረጃ ምንጫችን አያይዘው ነግረውናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል በተፈጠረው የግንኙነት መሻከር ምክንያት በዐቢይ አህመድ መንግሥት ይደገፋል የሚባለው ብርጌድ ንሓመዱ፣ እንዲሁም የህወሓትን መሰንጠቅ ተከትሎ ከህወሓት የወጡ የትግራይ ታጣቂዎች በአፋር ክልል ውስጥ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴና ወታደራዊ ስልጠና ጀምረዋል።
በሌላ በኩል የአፋር ታጣቂዎች በትግራይ እና ኤርትራ አካባቢዎች ተመሳሳይ የትጥቅ እንደጀመሩ የሚያሳዩ መረጃዎች በየጊዜው በመውጣት ላይ ይገኛል። ይሄንን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ፖለቲካ እና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ የጅኦፖለቲካዊ ለውጦች ከመፈጠራቸው ጋር ተያይዞ የአፋርን ክልል እና ህዝብ የጦርነት ቀጠና የሚያደርጉ አዝማሚያዎች በመታየት ላይ ይገኛሉ።
በመሰል ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዐቢይ አህመድ እጅ እንደሚኖርበት የሚገመት ሲሆን፣ ነገሮች እየተባባሱ የሚቀጥሉ ከሆነ ሁኔታው በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ የማያባራ ጦርነት እየተደገሰ ስለመሆኑ የተለያዩ የፖለቲካና እና የአማፂ ኃይሎች ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች ግልፅ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።


