Sunday, May 3, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችከሱዳን ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ታጣቂዎች በዓባይ ግድብ አቅራቢያ ጥቃት...

ከሱዳን ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ታጣቂዎች በዓባይ ግድብ አቅራቢያ ጥቃት መፈፀማቸው ተነገረ።

ሰኔ 21/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!

በሱዳን ብሉናይል ግዛት ወታደራዊ ስልጠናው ወስደው በቅርቡ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የገቡ በርካታ ታጣቂዎች በዓባይ ግድብ ዙሪያ ጥቃት መፈፀማቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።

እነዚሁ ከሱዳን ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ታጣቂዎች ከጥቂት ቀናት በፊት በዓባይ ግድብ ዙሪያ በሚገኙ ሁለት ስፍራዎች ላይ ጥቃቶችን የፈፀሙ ሲሆን፣ በጥቃቱ በርካታ ንፁሃን እንደተገደሉ እና በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተነግሯል።

ጥቃት ከተፈፀመባቸው ቦታዎች አንዱ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው ልዩ ስሙ ቆታ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ በተጠቀሰው አካባቢ በፈፀሙት ጥቃት 14 ንፁሃን ዜጎችን ገድለው 6 ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል ተብሏዋል። 

ከቆታው ጥቃት ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በዓባይ ግድብ አቅራቢያ በሚገኝ የፌዴራል ፖሊስ ሶስተኛ ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢው ታጣቂዎቹ በተሽከርካሪ ላይ በፈፀሙት ጥቃት አሽከርካሪውን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ወደ 170 የሚገመቱ በሱዳን ብሉናይል ግዛት ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መዝለቃቸውን፣ ዞብል ፖስት በግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባጠናቀረው ዘገባ መግለፁ ይታወሳል።

ከሱዳን ስልጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ በዓባይ ግድብ ዙሪያ ባሉ ሁለት ቦታዎች ተከታታይ ጥቃቶችን የፈፀሙት ታጣቂዎች የጉሙዝ ተወላጆች እና ሌሎች የአረብኛ ተናገሪዎች መሆናቸውን ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል። 

የዓባይ ግድብን ለመጠበቅ እንደ አዲስ ተዋቅሯል የተባለውን የህዳሴ ኮር የኮማንዶ ኃይልን ጨምሮ፣ ጥቃቶቹ ከተፈፀሙባቸው ቦታዎች በቅርብ ርቀት የሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባት ለጥቃት አድራሾቹ ምንም አይነት ምላሽ አለመስጠታቸውን መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልፀዋል።

የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያን፣ ሱዳንን፣ እና ግብፅን ለዓመታት ሲያወዛግብ የኖረ ፕሮጀክት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሱዳን ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በግድቡ አቅራቢያ ጥቃት የፈፀሙት ታጣቂዎች እንደ ግብፅ ካሉ የውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይንቀሳቀስ የነበረው እና በቅርቡ ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረመው የቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ፣ ሱዳን ውስጥ ወታደራዊ ሰፈር ገንብቶ በግብፅ መንግሥት ይደገፍ እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።    

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ባሳለፍነው ግንቦት ወር ከሱዳን ብሉናይል ግዛት ተነስተው የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የገቡ 170 የሚገመቱ ታጣቂዎችን በስልጠና፣ በቁሳቁስ፣ እንዲሁም በጦር መሳሪያ አቅርቦት በኩል የግብፅ ድጋፍ ሳይኖርበት እንደማይቀር ዞብል ፖስት በግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባጠናቀረው ዘገባ በወቅቱ መረጃውን ያደረሱንን ምንጮች ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች