Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮች"የራሳችን ሰዎች ከጀርባችን እየወጉንና የኦሮሞ ህዝብ በእኛ ተስፋ እንዲቆርጥ እየሰሩ ነው" አቶ...

“የራሳችን ሰዎች ከጀርባችን እየወጉንና የኦሮሞ ህዝብ በእኛ ተስፋ እንዲቆርጥ እየሰሩ ነው” አቶ ሽመልስ አብዲሳ!

ሰኔ 28/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰመስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሞ ልሂቃን ከሰሞኑ ባደረጉት ስብሰባ ላይ “የእኛ ያልናቸው ሰዎች ከጀርባችን እየወጉንና የኦሮሞ ህዝብ በእኛ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ እየሰሩ ነው” ማለታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስታ ገልጸዋል።

አቶ ሽመልስ ይሄንን የተናገሩት፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረና በቅርቡ በኢሊሊ ሆቴል ከፌዴራል እና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በዐቢይ አህመድ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ወቀሳና ውንጀላ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር ይሄንን ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ተነግሯል። 

በቅርቡ ለእስር የተዳረጉትን አቶ ታዬ ደንደዓን ጨምሮ፣ እንደ አቶ ጃዋር መሐመድ እና ዶክተር ሚልኬሳ ሚዳጋ ያሉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በዐቢይ አህመድ እና በብልፅግናው አገዛዝ ላይ ከፍተኛ ወቀሳና እና ውንጀላ እያቀረቡ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ይሄንን ተከትሎ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰመስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ “የእኛ ያልናቸው ሰዎች ከጀርባችን እየወጉን እና የኦሮሞ ህዝብ በእኛ ላይ ተስፋ ቆርጦ እንዲነሳሳ ተደራጅተው እየሰሩ ነው” በማለት በስበሰባው ላይ ለተገኙት የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና ወታደራዊ አመራሮች ገልጸዋል።

ጃዋር መሐመድ እና ሚልኬሳ ሚዳጋ ከሰሞኑ “ዐቢይ አህመድ ከዓመታት በፊት የአማራን ህዝብ አጠፋለሁ” እያለ ይነግረን ነበር፣ “ዐቢይ አህመድ ፋሽስት ነው” በማለት በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርበው መናገራቸው፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳስቆጣቸው መረጃውን ያጋሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

በኢሊሊ ሆቴል በተካሄደው ስብሰባ ረዘም ያለ ንግግር ያደረጉት አቶ ሽመልስ፣ “የኦሮሞን ህዝብ ቀና ብሎ እንዲሄድ ያደረግነው እኛ ነን፣ ከጀርባ የሚወጉን የራሳችን ሰዎች ዋነኛ ዓላማቸው በእጃችን የገባውን ስልጣን እና ወርቃማ ዕድል ለሌሎች አሳልፎ መስጠት ነው፣ ይሄንን ደግሞ በህይወት እያለን አንፈቅድም” ማለታቸውን የመፅሔታችን የመረጃ ምንጭ የስብሰባውን አጠቃላይ ድባብ ለዞብል ፖስት አብራርተዋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ “በዚህ ስብሰባ የኦሮሞ ህዝብ ላመጣው ለውጥ ከፍተኛ አበርክቶ ያላችሁና ይህ ትውልድ እንደ አባት የሚያያችሁ የኦሮሞ ባለውለታዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት የሚቃረኑ አስተሳሰቦችን የሚያንፀባርቁ የራሳችንን ሰዎች ልትመክሯቸውና ወደ ትክክለኛ መስመር ልታስገቡልን ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ከዚህም በተጨማሪ፣ “እኛን ከጀርባ ሆነው ለሚወጉን የራሳችን ሰዎች ስስ ልብ ያላቸው በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ባለሥልጣናት እንዳሉ እናውቃለን፣ ይሁን እንጅ የኦሮሞን ህዝብ ማንም ከእኛ መነጠል አይችልም” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ከአቶ ሽመልስ አብዲሳ የማጠቃለያ ንግግር ላይ መደመጡን፣ የኢሊሊን ሆቴል ስብሰባ አስመልክቶ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያጋሩን ምንጮች ለመፅሔታችን ገልጸዋል።  

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች