ሰኔ 28/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
በአማራ ክልሉ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ወደ ሀገር ቤት አንመለስም ማለታቸውን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር የሀብሩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሲሳይ መኮንን እና በስም ያልተጠቀሱ ሌላ አንድ የወረዳ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ወደ ሀገር ቤት አንመለስም ማለታቸውን ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ወደ ኢትዮጵያ አንመለስም ያሉት የሀብሩ ወረዳ አመራሮች በዱባይ የሚገኙ ሲሆን፣ የስራ ባልደረቦቻቸው ለምን ወደ ኢትዮጵያ እንደማይመለሱ ሲጠይቋቸው “የብልፅግናን መንግሥትን ተማምነን አንመለስም” ማለታቸውን ከባልደረቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አመራሮቹ ይሄንን ያሉት በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት በፋኖ እጅ እንዳንወድቅ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ጥበቃ ሊያደርጉልን የሚችሉበት አቅም ላይ አይደሉም በሚል እንደሆነ መረጃውን ያደረሱን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከአካባቢው በርካታ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች እና መምህራን ስራቸውን እየተው ወደ መካከለኛው ምስራቅ መሄዳቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች የወጡ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የወረዳው አመራሮች ሀገር ጥለው እየሸሹ ነው ተብሏል።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ከሀገር ከወጡ በኋላ አንመለስም ያሉትን የሀብሩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና ሌላኛውን የወረዳ አመራር በሌላ ይተካሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም መረጃውን ያደረሱን ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።


