ሰኔ 30/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
በአዲስ አበበ ከተማ ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች በመውጣት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ደግሞ በከተማዋ የሚደረገው እስር ተባብሶ መቀጠሉን ዞብል ፖስት ከመረጃ ምንጮች ሰምቷል።
የፌዴራል እና የከተማዋ ፖሊስ በርካታ ወጣቶችን በጅምላ እያሰሩ እና ወደ ተለያዩ ማጎሪያ ቤቶች እየወሰዱ እንደሆነ በአዲስ አበባ ተጠናክሮ የቀጠለውን የጅምላ እስር አስመልክቶ የአይን ዕማኞች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
ከሰሞኑ እየተደረገ ነው የተባለው የጅምላ እስር ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ የጅምላ እስሩ አድማሱን አስፍቶ በአማራ እና ኦሮሞ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ስለመሆኑ ተነግሯል።
ተባብሶ በቀጠለው የጅምላ እስር ሠላማዊ ዜጎች ከፋኖ፣ ኦነግ፣ እና ህወሓት ጋር ግንኙነት አላችሁ እየተባሉ በርካታ የአማራ፣ ኦሮሞ፣ እና ትግራይ ተወላጆች ላይ በስፋት እየተፈፀመ ሲሆን፣ በርካታ ኤርትራውያንም ለኤርትራ መንግሥት ትሰልላላችሁ በሚል በጅምላ እየታሰሩ እንደሆነ ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
የጅምላ እስሩ እየተካሄደ ያለው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ሲሆን፣ አፈሳው በዐቢይ አህመድ ቀጥተኛ ትዕዛዝ መሰረት እየተፈፀመ ስለመሆኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለመፅሔታችን ገልጸዋል።
በከተማዋ በፖሊስ የታፈሱ ወጣቶች በሳሪስ፣ ሐና ማርያም፣ መገናኛ፣ አዲሱ ገበያ፣ ጎሮ እና ሌሎች በአዲስ አበባ በሚገኙ እስር ቤቶች ተወስደው በጅምላ እየታሰሩ መሆኑን መረጃውን ለመፅሔታችን ያደረሱን የአይን ዕማኞች አያይዘው ገልፀዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው በጅምላ እየታሰሩ ያሉ ወጣቶች የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ለሚያደርገው ጦርነት እንደ አንድ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ሲሉ፣ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ለአብነት ያህል፣ ከአምስት ዓመታት በፊት ከህወሓት ጋር ጦርነት ሊደረግ ሲል በርካታ የትግራይ ተወላጆች በጅምላ የታሰሩ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት ሲታወጅም እንደዚሁ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።
የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች በጅምላ የሚወስዷቸውን ወጣቶች የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች፣ የሚከታተሏቸውን ሚዲያዎች እና የYouTube ቻናሎች፣ እንዲሁም የሚያዳምጧቸውን ሙዚቃዎች ከእጅ ስልኮቻቸው እየተቀበሉ እንደሚያጣሩም ተነገሯል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የፌዴራል ፖሊስ ባሳለፍነው ወር በአዲስ አበባ ከተማ የተመረጡ ቦታዎች ድንገተኛ ፍተሻ ያደረገ ሲሆን፣ ፍተሻው ለመፈንቅለ መንግሥት ዓላማ በከተማዋ የተከማቸ የጦር መሳሪያ አለ በሚል እንደነበር ዞብል ፖስት መዘገቡ ይታወሳል።


