Wednesday, May 6, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዘገባዎችአራት ኪሎበኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሁሉን አቀፍ ድርድር ሊደረግ መሆኑ ተነገረ።

በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሁሉን አቀፍ ድርድር ሊደረግ መሆኑ ተነገረ።

ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!

በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሁሉን አቀፍ ድርድር ሊደረግ መሆኑ ተሰምቷል። ይካሄዳል የተባለው ድርድር መንግሥትን፣ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ቡድኖችን፣ እና በኦሮሞ ፖለቲካ የሚሳተፉ ሌሎች ኃይሎችን ያካተተ እንደሆነ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።

በመንግሥት እና በኦሮሞ የታጠቁና ያልታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ይደረጋል የተባለውን ሁሉን አቀፍ ድርድር በተመለከተ፣ የአውሮፓ ሕብረት የአመቻችነት እና የአደራዳሪነት ሚናን እንደሚጫወት ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባሳለፍነው ግንቦት ወር ዐቢይ አህመድ በአውሮፓ የተለያዩ ሀገራት ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የጉብኝቱ አንዱ ዓላማ የአውሮፓ መንግሥታት በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ለሚደረገው ድርድር ድጋፍ እንዲያደርጉ ለመጠየቅ መሆኑን፣ በቅርቡ ይደረጋል የተባለውን ድርድር አስመልክቶ መረጃውን ያደረሱን የዲፕሎማቲክ ምንጮች አያይዘው ጠቁመዋል።

በዐቢይ አህመድ መንግሥት እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው የግንኙነት መሻከር ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚሉ ስጋቶች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ሲሆን፣ ሁኔታውን ተከትሎ በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ይደረጋል የተባለውን ድርድር ዐቢይ አህመድ የሀገር ውስጥ ተቀናቃኞቻቸውን ከጎናቸው ለማሰለፍ ታሳቢ ሳያደርጉ አልቀረም ተብሎ ይገመታል።

ሁሉን አቀፍ የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች ድርድር ይደረጋል ከተባለባቸው ምክንያቶች አንዱ “የኦሮሞ አንድነት አደጋ ላይ ወድቋል” በሚል ሲሆን፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችን በማግባባት ላይ የሚገኙት አቶ አባዱላ ገመዳ እና አቶ ግርማ ብሩ “ድርድሩ የሀገር ውስጥ ተቀናቃኞችን እና የውጭ ኃይሎችን በጋራ መታገል የሚል ውጤት እንዲኖረው ይጠበቃል” የሚል አቋም እንዳላቸው፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አብራርተዋል።     

ከዚህ ቀደም በዐቢይ አህመድ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል በተከታታይ ለሁለት ጊዜ በታንዛኒያ ድርድር ተደርጎ ሳይሳካ መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ሊደረግ የታቀደው ድርድር የዚሁ የከሸፈው ውይይት ሦስተኛ አካል እንደሆነ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።

በቅርቡ ይደረጋል የተባለውን ድርድር በፓርቲ ፖለቲካ የሚሳተፉ፣ የልታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች፣ እንዲሁም የታጠቁ ኃይሎች በጋራ ከመንግሥት ጋር ለድርድር እንዲቀመጡ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ፣ ከዚህ ቀደም ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር በታንዛኒያ ከተደረገው ድርድር ለየት እንደሚያደርገው ተነግሯል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለታቀደው ድርድር የአመቻችነት እና አደራዳሪነት ሚና ይጫወታል የተባለው የአውሮፓ ሕብረት፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አመራር የሆኑትን ፕሮፌሰር መራራ ጉዲናን አግኝቶ አነጋግሯል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና አመራር የሆኑበት ኦፌኮ፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “ከጅምሩ የጨነገፈ እና የዐቢይ አህመድን ስልጣን ለማራዘም የሚካሄድ ነው” በሚል በምክክሩ እንደማይሳተፍ ማሳወቁ ይታወሳል።   

የኦሮሞ አንድነት አደጋ ላይ ወድቋል በሚል በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሁሉን አቀፍ ድርድር እንዲካሄድ ሃሳብ በማመንጨት እና የተለያዩ የኦሮሞ ፖለቲከኞችንና ባለሀብቶችን ሰብሰቦ የማነጋገር ኃላፊነትን ይዘዋል የተባሉት አቶ አባዱላ ገመዳ እና አቶ ግርማ ብሩ በበኩላቸው፣ ከአውሮፓ ሕብረት ተወካዮች ጋር ሊካሄድ በታቀደው የድርድር ሂደት ላይ ያተኮረ ውይይት  ከሰሞኑ አድርገዋል ተብሏል።

በቅርቡ ይካሄዳል ለተባለው ሁሉን አቀፍ የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች ድርድር የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሦስት፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት አራት ተደራደሪዎችን እንደሚወክሉ ለመፅሔታችን የደረሰው የዲፕሎማቲክ ምንጮች መረጃ ያመላክታል። 

የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ፣ ለኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራሮች ስለ ድርድሩ ሁኔታ፣ ቦታ፣ እና የጊዜ ቀነ ገደብ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ መልዕክት መላካቸውን መረጃውን ለመጽሔታችን ያጋሩን የዲፕሎማቲክ ምንጮች አያይዘው ጠቅሰዋል።

በታንዛኒያ ለሁለት ጊዜ ተደርጎ ሳይሳካ የቀረው ድርድር ሦስተኛው አካል ነው በተባለው ድርድር የፌዴራል እና ኦሮሚያ ክልል ተወካዮቻቸውን የመረጡ ቢሆንም፣ በጃል መሮ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ግን እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የሰጠው ምላሽ እንደሌለ ተነግሯል።

ጃል መሮ የሚመራው ታጣቂ ቡድን ጃል ሰኚ ከመንግሥት ጋር መስማማቱን ተከትሎ “ዘመቻ ፅናት” የተሰኘ ወታደራዊ ዘመቻ አውጆ ከፌዴራል እና ኦሮሚያ ኃይሎች ጋር ውጊያ እያደረገ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ጦርነት አቁሞ በድርድሩ ይሳተፋል ወይስ ድርድሩን ውድቅ ያደርጋል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ይሆናል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ እነ አባዱላ ገመዳ እና ግርማ ብሩ እንደ ጃዋር መሀመድ ያሉ በውጭ ሀገር የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎችን ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ለማገናኘት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ፣ ይካሄዳል የተባለውን ሁሉን አቀፍ ድርድር አስመልክቶ መረጃውን ያደረሱን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለዞብል ፖስት አክለው ገልጸዋል።

ዞብል ፖስት “ድርድሩን የት እና መቼ ለማካሄድ ታስቧል?” የሚል ጥያቄ ለዲፕሎማቲክ ምንጮች ያቀረበ ቢሆንም፣ የመረጃ ምንጮቻችን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች