ኅዳር 25/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና
የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዩ ወታደራዊ ድጋፍ ልታደርግ መሆኑን ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች የደረሰው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዩ ወታደራዊ ድጋፉን ያገኛል የተባለው ተቋሙ እያሰለጠነ ለሚገኘው አዲስ የፀረ ሽምቅ እና ፀረ ሽብር የኮማንዶ ኃይል ሲሆን፣ ከተባበሩት አረብ ኢመሬቶች የሚገኘው ወታደራዊ ድጋፍ የፀረ ሽምቅ እና ፀረ ሽብር ኃይል አባላት ስልጠናቸውን ሲጨርሱ ለሚሰጣቸው ልዩ ስምሪት ግብዓት የሚውል መሆኑን መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።
በቅርቡ ይመረቃሉ ለተባሉት የኮማንዶ ኃይል አባላት ግልጋሎት የሚሰጡ የልዩ ኦፕሬሽን ሔሊኮፕተሮች እና የቅኝት ድሮኖች የተባበሩት አረብ ኢመሬቶቾ ለፌዴራል ፖሊስ ከምታደርገው ልዩ ወታደራዊ ድጋፍ ዋነኞቹ መሆናቸውን ዞብል ፖስት ያገኘው መረጃ ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ ለወታደራዊ አገልግሎቶች የሚውሉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችም ለተቋሙ በድጋፍ መልክ ይቀርባሉ ተብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፌዴራል ፖሊስ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ልዩ ወታደራዊ ስምሪት ለሚሰጣቸው የፀረ ሽምቅ እና ፀረ ሽብር የኮማንዶ ኃይል አባላት ከስድስት ወራት ለሚቆይ ጊዜ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን፣ አባላቱ ስልጠናቸውን ሲጨርሱ ልዩ ወታደራዊ ስምሪት እንደሚሰጣቸው ተነግሯል።
እንደ ዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች የፌደራል ፖሊስ በቁጥር ከፍተኛ ኃይል በማሰልጠን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በጊዜ ሂደት ከክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር የመከላከያን ቦታን ተክቶ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች በሚካሄዱ ጦርነቶች ላይ ዋነኛ ተዋናይ እንዲሆን በመንግሥት በኩል ዕቅድ ተይዟል።
የመከላከያ ሠራዊቱ እንደ ፋኖ እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ካሉ የታጠቁ ኃይሎች ጋር የሚያደርገውን ውጊያ ትቶ ወደ ብሔራዊ ጉዳዮች እንዲያተኩር በመንግሥት አቅጣጫ የተሰጠ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ ዝግጅት ከዚሁ ጋር የሚያያዝ መሆኑ ተነግሯል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ የመከላከያ ሠራዊቱ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ ባሳለፍነው መስከረም ወር አጋማሽ በደብረብርሃን፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ እና ባህርዳር ከተሞች ከአማራ ክልል ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት “መከላከያ ሠራዊቱን ለሌላ ግዳጅ ልናዘጋጅ ስለሆነ የአማራ ክልልን ፀጥታ በራሳችሁ አቅም ለመቆጣጠር መስራት አለባችሁ!” ማለታቸውን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።


