Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር ከአሥር ሺህ በላይ ሠራተኞችን ከስራ ሊያባርር ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር ከአሥር ሺህ በላይ ሠራተኞችን ከስራ ሊያባርር ነው።

ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም-ዞብል ፖስት ዜና!

የአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር በያዝነው የበጀት ዓመት ከአሥር ሺህ በላይ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን ከስራ ሊያባርር እንደሆነ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።

የከተማ መሥተዳድሩ ይሄንን ውሳኔ ያሳለፈው በ2017 ዓ.ም የበጀት መዝጊያ ላይ ሲሆን ውሳኔው በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆንና በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ተቀጣሪዎች ከስራ ገበታቸው እደሚሰናበቱ ተሰምቷል።

የመንግሥት ሠራተኞቹ ከስራ ገበታቸው የሚሰናበቱት በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን፣ የከተማ አሥተዳደሩ አላስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ቢሮዎች እዘጋለሁ ማለቱ ለሚባረሩ ሠራተኞች ከፍተኛ ቁጥር የሚይዘው ምክንያት እንደሆነ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የሠራተኞች “ብወዛ” እንዲካሄድ እንደተወሰነ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ አሰራር ውስጥ ለከተማ መስተዳሩ ፍላጎት የማይመቹና ፖለቲካዊ ስጋት እንደሚፈጥሩ የተፈረጁ እንደዚሁም “አላስፈላጊ ናቸው” በተባሉ የስራ መደቦች ላይ የሚሰሩ ሠራተኞች ከአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር ቅጥር እንደሚሰናበቱ የመረጃ ምንጮቻችን አያይዘው ጠቅሰዋል።

ይሄኛው ሠራተኞቹ የሚባረሩበት ምክንያት በዋናነት የአማራ ተወላጆችን እና የከተማዋን ነባር ነዋሪዎች እና ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት አላቸው በተባሉበት የከተማ መሥተዳድሩ ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ መሆኑም ታውቋል፡፡

የከተማ መሥተዳድሩ ውሳኔ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ የሚሰሩ ሠራተኞችን ጨምሮ የሚያሰናብት ሲሆን፣ ከስራ ሰዓት በኋላ በሆቴሎች ደጅ ፌስታል ይዘው ተመላሽ ምግብ እንደሚጠይቁ የሚነገርላቸውና በኑሮ ፈተና ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ ከስራ ገበታቸው ይባረራሉ ተብሏል።

ውሳኔው ከስራ ገበታቸው የሚባረሩ የዝቅተኛ ኑሮ የሚመሩ ሠራተኞችን ከነቤተሰቦቻቸው ከዚህ ለከፋ የኑሮ ፈተና እንደሚጋልጣቸው ምንጮቹ ስጋታቸውን አያይዞው አስረድተዋል።

የዐቢይ አህመድ መንግሥት ለበርካታ የመዝናኛ ስፍራዎች እና ለቅንጡ ፕሮጀክቶች ከሁለት ትሪሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን እና የዓለማችንን ውድ ጦርነቶች እየፈበረከ መቀጠሉ የሚታወቅ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር የሠራተኞች ቅነሳ ውሳኔ ራሱን “ሰው ተኮር” ብሎ የሚገልጸው ገዥ ፓርቲ በተግባር ሲገለጽ ኢ-ሰዋዊ ለመሆኑ ምስክር ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

መንግሥት በከተሞች ሊነሳ ይችላል ብሎ ለሚገምተው ሕዝባዊ ዓመፅ፣ ከኑሮ ውድነት፣ የሠላም እጦትና ሌሎች አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች በተጨማሪ፣ ከሰሞኑ የተላለፈው የሠራተኛ ቅነሳ ውሳኔ ለተፈራው ሕዝባዊ ዓመፅ ተጨማሪ ገፊ ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች