Saturday, October 24, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዜናዋና ዋና ዜናጅቡቲ በሙሳ አሊ ተራራ ወታደራዊ ስምሪት ልታደርግ ነው።

ጅቡቲ በሙሳ አሊ ተራራ ወታደራዊ ስምሪት ልታደርግ ነው።

ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም ዞብል ፖስት ዜና! 

ጅቡቲ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚያዋስናት የሙሳ አሊ ተራራ ዙሪያ ወታደሮቿን ልታሰፍር እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።

አካባቢው የኢትዮጵያን አፋር ክልል፣ የኤርትራን ደቡባዊ ቀይ ባህር ክፍል፣ እንዲሁም የጅቡቲን ታጁራ ግዛት የሚያካልል የሦስትዮሽ አዋሳኝ ቀጠና ሲሆን፣ ጅቡቲ ጦሯን የምታሰፍረው በአፍሪካ ቀንድ እየታዩ ካሉ ለውጦች ጋር ተያይዞ ነው። 

የጅቡቲ መንግሥት ጦሩን በሙሳ አሊ ተራራ ወታደራዊ ስምሪት እንዲያደርግ የወሰነው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ፍጥጫ እየተካረረ መምጣቱን ተከትሎ እንደሆነ የመረጃ ምንጫችን ለመጽሔታችን አያይዘው ገልጸዋል።

ከጅቡቲ የሙሳ አሊ ተራራ ወታደራዊ ስምሪት ጋር በተገናኘ የፈረንሳይ መንግሥት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ በርካታ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጉን የመረጃ ምንጫችን ለመጽሔታችን አክለው ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት ከሰሞኑ ለጅቡቲ የአሥር ሚሊዮን ዩሮ ወታደራዊ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፉ ጅቡቲ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ወታደራዊ ኃይሏን እንድታጠናከር ታሳቢ ያደረ መሆኑ ተነግሯል።

ጅቡቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድንበር አዋሳኞች ተከታታይነት ያለው ወታደራዊ ቅኝት እያደረገች ሲሆን፣ ባሳለፍነው ጥር ወር መጨረሻ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ ልዩ ስሙ ኤሊዳዓር ወረዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የድሮን ጥቃት መፈፀሟ ይታወሳል።

በጥቃቱ ስምንት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ የጅቡቲ መንግሥት የገደልኩት የአንድነትና ዴሞክራሲ አስመላሽ ግንባር (FRUD) የታጣቂ ቡድን አባላትን ነው ሲል የአፋር ተወላጆች ደግሞ ንፁሐን ነው የተገደሉት በማለት ተቃውሞ ማሰማታቸው አይዘነጋም።

ጅቡቲን ጨምሮ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ በርካታ የአፋር ተወላጆች የሚገኙ ሲሆን ከሦስቱም ሀገራት በአፋር ስም የተቋቋሙ የታጣቂ ቡድኖች ሦስቱን ሀገራት በሚያዋስኑ ድንበሮች እንደሚንቀሳቀሱ የሚጠቁሙ በርካታ መረጃ አሉ።

የቀይ ባህር አፋሮች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር፣ እንዲሁም የአንድነትና ዴሞክራሲ አስመላሽ ግምባር (FRUD) ኤርትራን፣ ኢትዮጵያን፣ እና ጅቡቲን በሚያዋስኑ የሦስትዮሽ ድንበሮች የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ኃይሎች ናቸው።

የጅቡቲ መንግሥት በሙሳ አሊ ተራራ ወታደራዊ ስምሪት ያደርጋል የተባለው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እና በአካባቢው የሚደረጉ የታጣቂ ኃይሎች እንቅስቃሴ አሳስበውኛል በሚል እንደሆነ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች