Friday, May 8, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየሠላም ስምምነት ተቀብለው ትጥቃቸውን ያወረዱ የጃል ሰኚ ሠራዊት አባላትን መንግሥት በቡድን እየረሸነ...

የሠላም ስምምነት ተቀብለው ትጥቃቸውን ያወረዱ የጃል ሰኚ ሠራዊት አባላትን መንግሥት በቡድን እየረሸነ መሆኑ ተነገረ።

ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!

በኦሮሚያ ክልል ርዕሰመስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና በጃል ሰኚ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ክንፍ የሠላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ስምምነቱን ተከትሎ ትጥቃቸውን ያስረከቡ በርካታ የሠራዊቱ አባላት በመንግሥት እየተገደሉ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።

በሕዳር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ከኦሮሚያ ክልል ጋር የተደረገውን የሠላም ስምምነት ተቀብለው ትጥቃቸውን ለመንግሥት ያስረከቡ በርካታ የጃል ሰኚ ሠራዊት አመራሮችና አባላት፣ በቅድሚያ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ እስር ቤቶች እንዲወሰዱ ከተደረገ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት በቡድን በቡድን እየተመረጡ በሌሊት እንደተረሸኑ የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።

ጃል ሰኚ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር የሠላም ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ በቡድን በቡድን የተረሸኑት ታጣቂዎች በትጥቅ ትግል ወቅት የዞን እና የወረዳ ባለሥልጣናትን ገድለዋል በሚል የተጠረጠሩ መሆናቸውን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

የተረሸኑት የጃል ሰኚ ሠራዊት አመራሮችና አባላት ትጥቃቸውን ካወረዱ በኋላ በቅድሚያ በኦሮሚያ ክልል አምቦ እና ሰንቀሌ በሚገኙ እስር ቤቶች ታስረው እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን፣ መንግሥት እንዲገደሉ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ከእስር ቤቶች እየተወሰዱ በሌሊት መረሸናቸውን መረጃውን ያደረሱን ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።

ከተረሸኑት የሠራዊቱ አመራሮች እና አባላት በተጨማሪ በዞን እና ወረዳ ባለስልጣናት ላይ ግድያ ፈፅመዋል የተባሉ ሌሎች የቀድሞ ታጣቂዎች ደግሞ በሟች ባለሥልጣናት ቤተሰቦች ክስ እንዲመሰረትባቸው የተደረጉ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ከ13 እስከ 24 ዓመት እስራት እንደፈረደባቸው ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያመላክታል።

በሌላ በኩል ከመንግሥት ጋር የተደረገውን የሠላም ስምምነት ተከትሎ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የተደረጉ ሌሎች የሠራዊቱ አመራርና አባላት መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ለእያንዳንዳቸው በሲንቄ ባንክ አካውንት 90 ሺህ ብር መልሶ መቋቋሚያ እንዲሰጣቸው ከተደረገ በኋላ አካውንቶቻቸው መልሰው እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉን የመረጃ ምንጫችን ለመጽሔታችን አስረድተዋል።

የመልሶ መቋቋሚያ ገንዘብ ተሰጥቷቸው አካውንታቸው የታገደባቸው የቀድሞ ሠራዊት አባላት ገንዘቡን ጃል ሰኚ እንዲያስለቅቅላቸው ቢጠይቁም ጃል ሰኚ ምንም አይነት ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ይመራው የነበረው ሠራዊት አባላት በቀድሞው አለቃቸው ክህደት ተፈፅሞብናል እያሉ እንደሚገኙ ተነግሯል።

ከቡድናዊ ርሸና፣ ከረዥም ዓመታት የእስር ፍርድ፣ እና በመልሶ ማቋቋም ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ከተደረጉት የተረፉ እና በመንግሥት እምነት የተጣለባቸው ቀሪ የጃል ሰኚ ሠራዊት አባላት ደግሞ፣ ወደ ኦሮሚያ ክልል የፀጥታ መዋቅር እንዲገቡ መደረጉን መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

ጃል ሰኚ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር የሠላም ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ በጃል መሮ የሚመራው ሠራዊት “ዘመቻ ፅናት” የሚል ወታደራዊ ዘመቻ አውጆ ከኦሮሚያ ክልል እና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመላው ኦሮሚያ ጦርነት እያደረገ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች