ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም—ዞብል ፖስት ዜና!
በኦሮሚያ እና ሶማሊያ ክልሎች አዋሳኝ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ግጭት መቀስቀሱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ባለፍነው ሳምንት በሁለቱ ክልሎች መካከል የድንበር ግጭት ተቀስቅሶ የነበረ ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ አራት ታዳጊዎችን ጨምሮ የስድስት ንጹሃን ሕይወት ማለፉን ቢቢሲ የኦሮምኛ ዜና ክፍል መዘገቡ ይታወሳል።
በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች መካከል በድጋሜ የተቀሰቀሰው ግጭት ከመጀመሪያው የከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ ንፁሐንን ጨምሮ ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በሁለቱ ክልሎች ባለፈው ሳምንት ግጭት የተቀሰቀሰው የሶማሌ ክልል ተወላጆች ድንበር ተሻግረው በምሥራቅ ቦረና ዞን በዋጪሌ ወረዳ ቦጂ ቀበሌ ሕገወጥ ሠፈራ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል በሚል እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በግጭቱ በሶማሌ ክልል አዋሳኝ በምትገኘው “ራሮ” ቀበሌ በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።
በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች መካከል በአንድ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ግጭት የተቀሰቀሰው ዛሬ ንጋት ላይ ሲሆን፣ ራሮ ተብላ በምትጠራው የሁለቱ ክልልሎች አዋሳኝ አቅራቢያ በሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉንና ሰብአዊ ጉዳት መድረሱን የመረጃ ምንጫችን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት የተቀሰቀሰውን የድንበር ግጭት ተከትሎ የሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ 12 የኦሮሚያ እንዲሁም 4 የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች መገደላቸው ተነግሯል። ከታጠቁ ኃይሎች በተጨማሪ ከ20 በላይ ንፁሃን በግጭቱ መገደላቸውን የመረጃ ምንጫችን አያይዘው ገልጸዋል።
ሁለቱ ክልሎች በተለያዩ ጊዜያት ደም አፋሳሽ የድንበር ግጭት ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ እና ሶማሌ ክልል ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው እና በርካቶች ህይወታቸውን ማጣታቸው አይዘነጋም።


