Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዘገባዎችየምርመራ ዘገባ"ተቋሙ የመንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የተደረገበት ዘመን አብቃቷል" የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር...

“ተቋሙ የመንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የተደረገበት ዘመን አብቃቷል” የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ።

ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም– ዞብል ፖስት የምርመራ ዘገባ! 

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ተደርገው የተሾሙት አቶ ብርሃኑ አዴሎ የስራ አመራር በሚሰጡበት ጊዜ “ተቋሙ የመንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ እንዲሆን የተደረገበት ዘመን አብቅቷል” ማለታቸውን ዞብል ፖስት ከተቋሙ ባገኘው መረጃ አረጋግጧል።

አቶ ብርሃኑ አዴሎ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ አስተዳድር ዘመን በሚንስትርነት ማዕረግ የካቤኔ ጉዳዮች ኃላፊ በመሆን ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሰኔ ወር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ተደርገው ሲሾሙ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር አባላት ጀምሮ እስከ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድረስ ግለሰቡ “የፖለቲካ ውግንና አላቸው” በሚል ሹመታቸው ከፍተኛ ቅሬታን ሲያስተናግድ ተስተውሏል።

የአቶ ብርሃኑ አዴሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ተደርጎ መሾምን ተከትሎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ በሚያደርጉ ግለሰቦች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ሁኔታው መነጋገሪያ እንደነበር አይዘነጋም።

ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ “የምመራው ተቋም እንደከዚህ ቀደሙ የመንግሥትን ስም ለማጥፋት እና የሀገርን ገፅታ ለማጥፋት እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ አይቀጥልም፣ ያ ጊዜ አብቅቷል” ማለታቸውን ዞብል ፖስት ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የተቋሙን ሠራተኞች አነጋግሮ ባጠናቀረው በዚህ የምርመራ ዘገባ አረጋግጧል።

አዲሱ ተሿሚ ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ አንስቶ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቀደም ብሎ ጥናት እና ምርምር የጀመረባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቋረጡ እና በሪፖርት እንዳይካተቱ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን መጽሔታችን ያነጋገራቸው አንድ የተቋሙ ጥናት ክፍል ሠራተኛ ገልጸዋል።   

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ፣ “ተቋሙ እንዲቋረጡ ያደረጋቸውን ምርመራዎች ለውጪ የሰብዓዊ መብት ተቋማት አሳልፋችሁ ሰጥታችኋል” በሚል በተቋሙ ውስጥ በተመራማሪነት ለተመደቡ ሙያተኞች ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ላይ ያተኮሩ አዳዲስ ክስተቶች ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ለተቋሙ ሪፖርት ሲደረጉ፣ በተቋሙ ተቀጥረው የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች “እንደከዚህ በፊቱ ጉዳዮችን በራሳቸው መንገድ ከማጣራት እንዲታቀቡ እና በመንግሥት ትዕዛዝ ብቻ እንዲሰሩ” አቅጣጫ መሰጠቱን ዞብል ፖስት ያነጋገራቸው ሌላኛው የተቋሙ ሠራተኛ ገልጸዋል። 

ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው፣ “በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከማጣራት እና ከማጋለጥ ይልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለሚፈጽመው መንግሥት ተባባሪ ሆኗል” ተብሏል።

ባሳለፍነው ዓመት ከኃላፊነታቸው የተነሱት ዶክተር ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በሚመሩበት ወቅት፣ በተቋሙ የሚወጡ ሪፖርቶች ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭ መንግሥታት እና ዓለምአቀፍ ተቋማት ጭምር ተቀባይነት የነበራቸው ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን ተቋሙ ምንም አይነት ተዓማኒነት የሌለው እና መንግሥት በኢትዮጵያ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዳይጋለጡ አፈና የሚፈፅምበት ሁነኛ መሳሪያ መደረጉን ይሄንን ዘገባ ለማጠናቀር ያነጋገርናቸው የተቋሙ ምንጮች ገልጸዋል።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም በሀገሪቷ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፀም ቅድመ-ሪፖርት እና ዝርዝር የጥናት ውጤቶችን አከታትሎ በማቅረብ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ሲታሰሩ ድርጊቱን በአፋጣኝ በማውገዝ መግለጫ የሚያወጣ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ተመሳሳይ ክስተቶች እየተፈጠሩ ቢሆንም “ተቋሙ ክስተቶችን በዝምታ የሚመለከትበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ የተቋሙን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ መረጃውን ያጋሩን ምንጮች ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ስራቸውን በነፃነት ይሰሩ የነበሩ የተቋሙ ሠራተኞች አሁን ላይ አገዛዙ ከፍተኛ ክትትል እያደረገባቸው እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ይሄንኑ ተከትሎ በርካታ የተቋሙ ሠራተኞች ከስራ ገበታቸው ለመልቀቅ ሌሎች አማራጮችን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኙ የመረጃ ምንጫችን ተቋሙ የደረሰበትን አስከፊ ደረጃ አስረድተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር ዓቀፍ እና ዓለምአቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ ጥናቶችን የሰሩ እና ሪፖርቶችን ያጠናቀሩ የነበሩ የተቋሙ ሠራተኞች፣ አሁን ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት “ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ እና ማስፈራሪያ” እንደሚደርሳቸው ዞብል ፖስት ለዚህ የምርመራ ዘገባ ያነጋገርናቸው ከዚህ በፊት በሰፋፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ በተመራማሪነት የሰሩ የተቋሙ ሠራተኛ ባደረሱት መረጃ አረጋግጠዋል።

ሁኔታውን አስመልክቶ ባሳለፍነው ሰኔ ወር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ተደርገው የተሾሙት አቶ ብርሃኑ አዴሎ መሰል የአፋናና ማስፈራሪያ መልዕክቶች ለተቋሙ ሠራተኞች ሲላክ ከለላ ከመስጠት ይልቅ ለአገዛዙ ባለሥልጣናት ተባባሪ እየሆኑ እንደሚገኙ እኚሁ የመረጃ ምንጫችን አያይዘው ጠቁመዋል።

ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚደርስባቸውን ማስጠንቀቂያ እና ማስፈራሪያ ተከትሎ፣ ለረፍት የወጡ የተቋሙ ሠራተኞች ወደ ስራ ገበታ አለመመለሳቸውን እንዲሁም ለሥራ ጉዳይ ወደ ውጭ የሄዱ ነባር የተቋሙ ሠራተኞችም በሄዱበት ሀገር መቅረታቸውን የመረጃ ምንጫችን ለመጽሔታችን ያደረሱት መረጃ ያሳያል።

ከተቋሙ ሠራተኞች መልቀቅ ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እና የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ባሳለፍነው ወር ቀደም ብለው በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባታቸው አይዘነጋም። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ከሰኔ 2011 ዓ.ም አንስቶ ለአምስት ዓመታት በኮሚሽነርነት ሲመሩ የቆዩት ዶክተር ዳንኤል በቀለ ከአንድ ዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አማካኝነት ከኃላፊነታቸው መሰናበታቸው የሚታወስ ነው።

የቀድሞው የተቋሙ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል የዜጎች መብት እንዲከበር ከመጠየቅ እስከ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሪፖርቶችን ማውጣት የደረሱ ስራዎችን ሲያከናውን የቆዩ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

አዲሱ ኮሚሽነር ከዚህ ቀደም በዶክተር ዳንኤል አመራርነት ዘመን በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰሩ ስራዎችን ነው “የተቃዋሚ ፓርቲ ስራ” በማለት የገለጹት።

የተቋሙን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ሃሳባቸውን ለዞብል ፖስት የሰጡት የተቋሙ ሠራተኛ፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋሙ በመንግሥት ተፅዕኖ ስር ሙሉ በሙሉ የወደቀ እና የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት የተሳነው ነው” በማለት ከዚህ በፊት የነበረው የተቋሙን አፈፃፀም አሁን ካለው ጋር በማነፃፀር ተቋሙ የደረሰበትን ውድቀት አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ እየተሸረሸረ ከመጣው የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ጋር በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን ለዓመታት በዋናነት ዳይሬክተርነት ይመሩ የነበሩት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ከመንግሥት በሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ጫና እና ዛቻ ምክንያት ባሳለፍነው ሐምሌ ወር መገባደጃ ላይ ከኃላፊነት ለመልቀቅ መገደዳቸውን ማሳወቃቸው አይዘነጋም።

አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ከኃላፊነታቸው የለቀቁበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ ከአንድ ዓመት ወዲህ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ባሉ ሚዲያዎች እየቀረቡ በኢትዮጵያ ስለሚፈፀሙ የሰብዓዊ  መብት ጥሰቶች በሚሰጧቸው መግልጫዎችና ማብራሪያዎች፣ እንዲሁም በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ዜጎችን ስለ ሰብዓዊ መብቶች በሚሰጧቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች ምክንያት የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከፍተኛ ጫና እያደረገባቸው እንደሚገኝ መግለጻቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ በመጪው ዓመት ሀገር አቀፍ ምርጫ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት በምርጫ ሂደቱ ወቅት ሊፈፀሙ የሚችሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና አፈናዎችን በንቃት ሊከታተሉ እና ሊያጋልጡ የሚችሉ ተቋማትን በማዳከም ላይ ይገኛል።

ይሄንን ተከትሎ፣ መንግሥት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር እና ተፅዕኖ ስር እንዲወድቅ ከማድረግ ጀምሮ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ አፋኝ ሕጎችን እስከ ማውጣት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን እና ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ጫና እስከመፍጠር የደረሰ ግልጽ የአፋር እንቅስቃሴ ውስጥ ላይ ይገኛል።

ሁኔታው ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከሚፈፀሙባቸው ሀገራት ከፊት ቀድመው ከሚጠሩ አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከዚህ በፊት ከነበረው የከፋ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ሊያስከትል እንደሚችል የብዙዎች ስጋት ነው። 

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች