Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዜናዋና ዋና ዜናኢትዮጵያ የሶማሌላንድ አየር ኃይል አባላትን ልታሰለጥን ነው። 

ኢትዮጵያ የሶማሌላንድ አየር ኃይል አባላትን ልታሰለጥን ነው። 

ነሐሴ 17 2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና! 

ኢትዮጵያ የሶማሌላንድ አየር ኃይል አባላትን ልታሰለጥን መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል። ራስ ገዝ የሆነችው ሶማሌላንድ የአየር ኃይል ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሯን ተከትሎ ነው ኢትዮጵያ አባላቱን እንደምታሰለጥን የተነገረው።

ዓለምአቀፍ የሀገርነት እውቅናን በማፈላለግ ላይ የምትገኘው ሶማሌላንድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደ አሜሪካ ካሉ ኃያላን ሀገራት የሀገርነት እውቅናን ሊሰጧት እንደሚችሉ የሚጠቆሙ በርካታ ማሳያዎች እየታዩ ሲሆን፣ ሀገሪቷ ከዚህ ቀደም ያልነበራትን አየር ኃይል ለማቋቋም ማሰቧ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

ሶማሌላንድ አየር ኃይል ለማቋቋም የጀመረችውን ጥረት እና ኢትዮጵያ ለአባላቱ ትሰጣለች የተባለውን ስልጠና የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች በገንዘብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደምታደርግ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ኤርትራ የሶማሊያን ወታደሮች እያሰለጠነች መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ግብፅ በኤርትራ ምድር ሃያ አንድ ሺህ የእግረኛ፣ ባሕር ኃይል፣ እንዲሁም ልዩ ኃይል የሶማሊያ ወታደሮች ለሚያደርጉት ስልጠና ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ተጨባጭ መረጃዎች ያሳያሉ።

ስልጠናው በዋናነት አዲስ የሚመሰረተውን የሶማሌላንድ አየር ኃይል የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን፣ ይሄንን የሚያስፈፅም የጋራ ግብረኃይል መቋቋሙን እና ንግግሮች መጀመራቸውን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

በፈረንጆቹ 2024 በዐቢይ አህመድ እና ሙሴ ብሄ መካከል በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ መካከል በአዲስ አበባ ተፈርሞ በቱርክ አንካራ ከተቀደደው የወደብ መግባቢያ ስምምነት ቀጥሎ፣ ኢትዮጵያ የሱማሌላንድን አየር ኃይል አብራሪዎች ታሰለጥናለች መባሉ አዲሱ የሱማሌላንድ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ኢሮ  ከመጡ ወዲህ ትልቅ ሊባል የሚችለው ለውጥ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም እና የሶማሌላንድ ወታደራዊ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ኢስማኤል ታኒ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የወደብ መግባቢያ ስምምነት በተፈራረሙ ማግስት በአዲስ አበባ ተገናኝተው መምከራቸው አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ከአየር ኃይል አባላት ቀድም ብሎ በርካታ የሶማሌላንድ ወታደሮችን ማሰልጠኗ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ አዲስ ይቋቋማል ለተባለው የራስ ገዟ ሶማሌላንድ አየር ኃይል አብራሪዎችን ለማሰልጠን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ ምንጮች ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የወደብ መስማሚያ ስምምነት ከተፈራረመችበት ጊዜ አንስቶ ከሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት ውጥረት የነገሰበት ሲሆን፣ የወደብ ስምምነቱ ቱርክ አንካራ ላይ ባሳለፍነው ዓመት ውድቅ የተደረገ ቢሆንም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት መሻሻል እንዳይታይበት የሚያደርጉ ሌሎች ቀጠናዊ ጉዳዮች እየተከሰቱ ይገኛሉ።

ኤርትራ እና ግብፅ በሶማሊያ በኩል፣ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች በሶማሌላንድ በኩል ተሰልፈው የሚያደርጉት ቀጠናዊ ሽኩቻ ለወትሮው ውጥረት የማያጣውን የአፍሪካ ቀንድ ወደባሰ ቀውስ ሊያስገባው እንደሚችል የበርካቶች ስጋት ነው። 

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች