ነሐሴ 20 2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
በአቶ ጌታቸው ረዳ የተመራ ቡድን እና የመከላከያ ሠራዊቱ ወታደራዊ ካውንስል ከሰሞኑ ውይይት ማድረጋቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ቡድኑ ከወታደራዊ ካውንስሉ ጋር ባደረገው ውይይት የትግራይ ክልልን እና ኤርትራን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ መስጠቱን እና የፌዴራል መንግሥት ኃይሉን በትግራይ ክልል እንዲሁም በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር እንዲያሰማራ መጠየቁን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ከህወሓት የተገነጠለውን አንጃ ቡድን የሚመሩት የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ የተሰኘ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋማቸው የሚታወስ ነው።
አቶ ጌታቸው ረዳ ከመከላከያ ሠራዊቱ ወታደራዊ ካውንስል ጋር በነበራቸው ውይይት ማብራሪያ የሰጡት ስምረት ፓርቲን አብረዋቸው ከመሰረቱ የቀድሞ የህወሓት አባላት ጋር መሆኑን መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች ጠቁመዋል።
አቶ ጌታቸው ህወሓትን ለመገዳደር ከመሰረቱት የፖለቲካ ፓርቲ በተጨማሪ፣ ከህወሓት የወጡ ታጣቂዎች እና ወታደራዊ መሪዎች ያቋቋሙት “የትግራይ የሠላም ኃይሎች” ከተሰኘው ታጣቂ ቡድን ጋር አብረው እንደሚሰሩም የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እነ አቶ ጌታቸው ረዳ ለመከላከያ ሠራዊቱ ከወታደራዊ ካውንስል ጋር በነበራቸው ውይይት በሁለት ዋና ዋና ወቅታዊ ጉዳዮች ትኩረት ማድረጋቸው ተነግሯ
በጌታቸው ረዳ የተመራው ቡድን ለወታደራዊ ካውንስሉ ማብራሪያ ከሰጠበባቸው ጉዳዮች የመጀመሪያው የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥቱ ሠራዊቱን በትግራይ ክልል እንዲያሰማራ ጠይቀዋል ተብሏል።
እንደ ማብራሪያው ከሆነ፣ የህወሓት አመራሮች በትግራይ ክልል ዞኖች አስተዳደሮችን በኃይል ለማፍረስ እየሰሩ ያሉት መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ሠራዊቱን በትግራይ ክልል ባለማሰማራቱ ምክንያት በመሆኑ ይህ ችግር በአስቸኳይ ሊቀረፍ ይገባል ተብሏል።
ጄኔራል ታደሠ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ በትግራይ ክልል የዞን መዋቅሮችን የማፍረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ተቃውሞ በመሰማት ላይ ይገኛል።
የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ከተፈረመ ሦስተኛ ዓመቱን የያዘ ቢሆንም በስምምነቱ ጦርነቱን ከማስቆም ውጭ የዐቢይ አህመድ መንግሥት የስምምነቱ አፈፃፀም እንዲዛዛና ተግባራዊ እንዳይሆን በማድረጉ ከተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ ወቀሳ ሲደርስበት ይስተዋላል።
በዚህም ትጥቅ ሊፈታ እና ሠራዊቱን ወደ ማኅበረሰቡ ሊቀላቅል የተስማማው ህወሓት ነባር ኃይሉን እያጠናከረ እና አዳዲስ ሠራዊት እያደራጀ የትግራይ ክልልን በኃይል መልሶ ለመቆጣጠር እየሞከረ እንደሚገኝ ከክልሉ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
እነ አቶ ጌታቸው ለወታደራዊ ካውንስሉ ማብራሪያ የሰጡበት ሌላኛው ጉዳይ ኤርትራን የሚመለከት ሲሆን፣ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው ከትግራይ ክልል በተጨማሪ መከላከያ ሠራዊቱ በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር በአስቸኳይ እንዲሰፍር ከወታደራዊ ካውንስሉ ጋር የተወያየው ቡድን መጠየቁ ተነግሯል።
በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ልሂቃን ቡድን ከዐቢይ አህመድ ጋር እንደፈጠረው ጥምረት ሁሉ በህወሓት እና ኤርትራ የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች መካከል ሌላ ጥምረት መመስረቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሁለቱም ጥምረቶች በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል አዲስ ጦርነት ሊያዋልዱ እንደሚችሉ የበርካቶች ስጋት ነው።
እነ አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልልና ኤርትራ ድንበር የመከላከያ ሠራዊቱ እንዲሰፍር የጠየቁ ቢሆንም፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ግን አብዛኛውን ሠራዊቱን በአማራ ሕዝብ ላይ በከፈተው ጦርነት እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች አሰማርቶ ይገኛል።
አገዛዙ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ጦርነትን እንደ ብቸኛ አማራጭ በመውሰዱ ምክንያት ለዓመታት በሀገር ውስጥ በሚካሄዱ ጦርነቶች እንዲሳተፍ የተደረገው ሠራዊት በአቅም እና ቁጥር የተዳከመ ስለመሆኑ ይነገራል።
በዚህ ምክንያት እነ አቶ ጌታቸው ረዳ ሠራዊቱ በትግራይ ክልል እንዲሁም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር እንዲሰማራ ለወታደራዊ ካውንስሉ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አልባ ሊሆን እንደሚችል የዐቢይ አህመድ የጦርነት ፖሊስ ውጤቶች ጠቋሚ ናቸው።


