Tuesday, May 5, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት "በፋኖ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ" አለ።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት “በፋኖ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ” አለ።

ነሐሴ 23 207 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ ባላቸው የፋኖ ኃይሎች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው እየተመረጡ በክልሉ ኢመደበኛ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው እና በገፍ መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።

ከግድያ እና መፈናቀል የተረፉ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ከሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶችን እንደሚያደርጉ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እርምጃ እወስዳለሁ ያለው በእነዚህ የአማራ ተወላጆች ላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት “በወለጋ የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ሠራዊት በአካባቢው ሕዝብ ላይ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በሕዝብ ያለውን ተቀባይነት በኃይል ለማሳጣት እየሞከረ ነው” ሲል በመግለጫው ክስ አቅርቧል።

ቡድኑ አያይዞም በወለጋ የሚንቀሳቀሰው ፋኖ የዐቢይ አህመድ ድጋፍ ያለው ነው በማለት የፈረጀ ሲሆን፣ ዐቢይ አህመድ ፋኖን አጠፋለሁ ብሎ ሁለት ዓመታት ሙሉ ጦርነት ካወጀበት ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ግን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ፍረጃ በእውነት ላይ የተመረኮዘ አለመሆኑን ያመላክታል።

ከሰሞኑ አፍሪካ ኢንተለጀንስ የተሰኘው የዜና ምንጭ በሀገረ አሜሪካ በተወካዮቻቸው በኩል የተደረጉ ውይይቶችን ተከትሎ በፋኖ እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተኩስ አቁም ተደርጓል ብሎ ማስነበቡ የሚታወስ ሲሆን፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በትናንትናው ዕለት ያወጣው መግለጫ ግን የዜና ምንጩን የመረጃ ትክክለኛነት ጥያቄ እንዲነሳበት አድርጓል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በመግለጫው እንዳስነበበው በወለጋ በሚንቀሳቀሰው ፋኖ ላይ እወስዳለሁ ባለው እርምጃ የወታደራዊ ዘመቻው ዒላማ የሆኑትን ሁሉ ከአካባቢው አፀዳለሁ ብሏል።

ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት መሰል ጥቃቶች ያልታጠቁ እና የመንግሥት ጥበቃ የሌላቸውን ንፁሐን ዒላማ ያደርጉ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ሁኔታው በንፁሐን ህይወት ላይ በተለይም በአማራ ተወላጆች ላይ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የብዙዎች ስጋት ነው።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች