ኅዳር 5/2018 ዓ.ም ዞብል–ፖስት ዜና!
የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች የውጭ ሀገራት ወታደሮችን ማሰልጠኛ የጦር ሰፈር በኢትዮጵያ እየገነባች መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወታደራዊ ምንጮች ለዞብል ፖስት ያደረሱት መረጃ ያሳያል።
ወታደራዊ ማሰልጠኛው እየተገነባ የሚገኘው በምዕራብ ኢትዮጵያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዳቡስ ወንዝ አቅራቢያ መሆኑን መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ጠቁመዋል።
የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች እንደገለፁት በተባበሩት አረብ ኢመሬቶች እየተቋቋመ የሚገኘውን ወታደራዊ ማሰልጠኛ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የወታደራዊ መረጃ እና ደኅንነት ሹሙ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና በሚስጥር ይመሩታል ተብሏል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚቋቋመው ወታደራዊ ማሰልጠኛ ስፍራ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የምህንድስና ባለሙያዎች የጫካ ምንጣሮና እና ቁፋሮ ስራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅት የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች ወታደራዊ መኮንኖችም በሔሊኮፕተር ወደ ስፍራው አቅንተው ጉብኝት ማድረጋቸውን ዞብል ፖስት ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ የመረጃ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያሳያል።
ወታደራዊ ማሰልጠኛው ስራ በሚጀምርበት ወቅትም እስከ አሥር ሺህ የሚደርሱ ወታደሮችን ማሰልጠን የሚያስችል ሲሆን፣ የሚቋቋምበት ዋነኛ ምክንያትም የውጭ ሀገር ወታደሮችን ለማሰልጠን ነው ተብሏል።
በዚህ የወታደራዊ ማሰልጠኛ የጦር ሰፈር በተባበሩት አረብ ኢመሬቶች ድጋፍ የሚደረግለት ጄኔራል ሀምዳን ዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ወታደሮች በዋነኛነት እንደሚሰለጥኑበት የተነገረ ሲሆን፣ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የሚሳተፉ ቅጥረኛ ወታደሮችም ስልጠና ይሰጣቸዋል ተብሎ እንደሚታሰብ የመረጃ ምንጫችን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሶማሌላንዱ የበበርበራ እና በኬኒያው ሞምባሳ ወደቦች በኩል በመቋቋም ላይ ለሚገኘው ወታደራዊ ማሰልጠኛው ግብዓት የሚሆኑ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና የጦር መሳሪያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ሲሉ የዞብል ፖስት ወታደራዊ ምንጮች ለመጽሔታችን አስረድተዋል።
የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ በፈረንጆቹ ነሐሴ 2023 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ከተፈራረሟቸው በርካታ ስምምነቶች አካከል በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረግ ትብብር አንዱ ሲሆን፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ይገነባል የተባለው የውጭ ሀገራት ወታደሮች ማሰልጠኛ ወታደራዊ ሰፈር የስምምነቱ አንዱ አካል ነው ተብሎ ይገመታል።


