ኅዳር 28/2018 ዓ.ም ዞብል ፖስት-የምርመራ ዘገባ!
በኢትዮጵያ ውስጥ፣ ልክ እንደ ማንነት ተኮር ጥቃቶች ሁሉ በሐይማኖት ተቋማት፣ በሐይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም በአማኞች ላይ ያነጣጠሩ ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶች በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ዕምነቶችን ዒላማ አድርገው ሲፈፀሙ መመልከት አዲስ አይደለም።
በእነዚህ ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶች፣ ቤተ ዕምነቶች ይቃጠላሉ፣ የሐይማኖት አባቶች እና የጥቃቱ ኢላማ የተደረገው ሐይማኖት ተከታዮች በአሰቃቂ ሁኔታ ከመገደል እስከ የከፋ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል። ይህ ችግር የኢትዮጵያ እና ሕዝቧ አንገብጋቢ ብሔራዊ አደጋ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል።
በኢትዮጵያ ከተፈፀሙ ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶች መካከል ካሳለፍነው የ2018 ዓ.ም ጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ኅዳር ወር የቀጠለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሐይማኖት አባቶች እና ምዕመናን ላይ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የተፈፀመው ሐይማኖት ተኮር ጥቃት አንዱ ነው። በርግጥ በአካባቢው መሰል ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶች መፈፀም ከጀመሩ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ መቆጠሩን የተለያዩ ተጨባጭ መረጃዎች ያሳያሉ።
ዞብል ፖስትም እንደ አንድ የኢትዮጵያን ሀገራዊ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድን ቀጠናዊ ጉዳዮች በንቃት እንደሚከታተልና ወሳኝ ክስተቶችን ለአንባቢያን እንደሚያቀርብ የዲጅታል መጽሔት፣ ለአንድ ወር ያክል የመረጃ ማሰባሰብ ተግባራትን ካከናወነ በኋላ በአርሲ ክርስቲያኖች ላይ የሚፈፀሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመዳሰስ ያለመውን ይሄንን የምርመራ ዘገባ አዘጋጅቷል።
የዚህ የምርመራ ዘገባ ዋነኛ ዓላማ ከቁጥር ባሻገር ያሉ ጉዳዮችን መዳሰስ ሲሆን፣ የዘገባው ዋነኛ ትኩረት በአርሲ እና አካባቢው በሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሐይማኖት አባቶች እና የሐይማኖቱ ተከታዮች ላይ ከሚፈፀሙ ጥቃቶች ጀርባ ያሉ እጆችን እና የጥቃቶቹን ፈፃሚዎች ፍላጎቶች አጥንቶ ለአንባቢያን ማቅረብ ነው።
የምርመራ ዘገባውን ለማዘጋጀት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን እና ተጨባጭ መረጃዎችን ሊሰጡን ከሚችሉ በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃለምልልስ አድርገናል። ከዚህም በተጨማሪ፣ መንግሥታዊ የሆኑ እና ያልሆኑ ተቋማት ያወጧቸውን ሪፖርቶች፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ሚዲያዎች ከሰሯቸው እና መጽሔታችን ትኩረቱን ካደረገበት ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዘገባዎችን በግብዓትነት ተጠቅመናል።
ዘገባውን ለማጠናቀር የተጠቀምናቸውን መረጃዎች ለማጋራት ፈቃደኛ ሆነው በቃለመጠይቁ የተሳተፉ ግለሰቦችን አስቀድመን እያመሰገንን፣ በጥያቄያቸው መሠረት ለእነሱም ሆነ ለቅርብ ቤተሰቦቻቸው ደኅንነት ሲባል ለዞብል ፖስት ጥያቄዎች ከሰጧቸው ምላሾች ውጭ ያሉ የቃለመጠይቁ ተሳታፊዎችን ማንነት እንዲሁም ማንነታቸውን ሊገልፁ የሚችሉ ተያያዥ ጉዳዮችን ከመጥቀስ ተቆጥበናል።
ጥቃቱ ሐይማኖት ተኮር ስለመሆኑ!
በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች እና የሐይማኖት አባቶች መገደላቸውን ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች የተለያዩ መግለጫዎች ተሰጥተዋል። ጥቃቱ የተፈፀመበትን የአርሲ ዞን የሚያስተዳድሩት አቶ ኢብራሂም ከድር በአካባቢው በክርስቲያኖች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት “ሐሰት ነው” በማለት ማስተባበላቸውን ቢቢሲ የአማርኛው ክፍል በጥቅምት 20 ይዞት በወጣው ዘገባ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበኩሉ ጥቃቱ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች አጣሪ ቡድን በመላክ ከጥቅምት 25 እስከ ጥቅምት 30 2018 ዓ.ም መረጃ አሰባስቦ “የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት” ያለውን ውጤት ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርጓል። አጣሪ ቡድኑም በኅዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ቀሪ የማጣራት ስራዎች እንደሚቀሩት በመጠቆም የአርሲው ጥቃት “ሐይማኖት ተኮር አይደለም” ብሏል።
ዞብል ፖስት የተለያዩ ወገኖችን አነጋግሮ ያገኘው ውጤት ግን የአርሲው ጥቃት ሐይማኖት ተኮር መሆኑን፣ እንዲሁም ጥቃቱን የፈፀሙት አካላት በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው እና የአልቃይዳ ምስራቅ አፍሪካ ክንፍ ከሆነው አልሸባብ ጋር ግንኙነት ያላቸው አክራሪ ታጣቂዎች መሆናቸውን ያሳያል። ይህም የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ ጥቃቱን ከካዱበት ምላሻቸው እንዲሁም ጥቃቱ ሐይማኖት ተኮር አለመሆኑን ካሳወቀው የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አቋም ፍፁም የተቃረነ መሆኑን ያሳያል።
መጽሔታችን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው የተለያዩ ወገኖች ጋር መረጃዎችን አሰባስቦ ካገኘው የምርመራ ውጤት መካከል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአርሲውን ጥቃት አውግዞ ካወጣው መግለጫ ላይ ከተነሱ አንዳንድ ሃሳቦች ጋር የሚያያዙ ውጤቶችን አግኝቷል። ምክር ቤቱ በጥቃቱ “ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ከክርስቲያኖች በተጨማሪ የተወሰኑ ሙስሊሞችም ተገድለዋል” ሲል በጥቃቱ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሐይማኖት አባቶች እና ተከታዮች በተጨማሪ የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮችም መገደላቸውን አሳውቋል።
ዞብል ፖስት ጥቃቱ ከተፈፀመባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የሸርካ ወረዳ አንድ ሰው አነጋግሮ ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በአርሲ የተለያዩ ወረዳዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች እና የሐይማኖት አባቶች በተለዬ ሁኔታ ኢላማ ተደርገው መገደላቸውን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ሁለት የእስልምና ሐይማኖት ተከታይ አባወራዎች ከወራት በፊት በኢትዮጵያዊ ወግ ጎረቤቶቻቸውን ከጥቃት ለመሸሸግ ሞክረዋል በሚል “ክርስቲያኖችን ከግድያ ልታስመልጡ ሞክራችኋል” ተብለው በአሳዛኝ ሁኔታ ተገድለዋል። ይህ መረጃ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮችም መገደላቸውን በመግለጫው ካሳወቀበት ክፍል ጋር የሚገናኝ ነው።
በሸርካ ወረዳ ከክርስቲያኖች በተጨማሪ በእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች ላይ የተፈፀመው ጥቃት እንደ አይኤስ አይኤስ፣ አልሸባብ፣ ወይም ቦኮሃራም ያሉ ኢስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች በሚገኙባቸው ሀገራት ውስጥ በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች “ርዕዮተ-ዓለማዊ አስተሳሰቦችን ተቃርነዋል ወይም ሕግ ተላልፈዋል” ባሏቸው ሙስሊሞች ላይ ከሚፈፅሙት የበቀል ግድያ ጋር የሚመሳሰል ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ኢላማ አድርጎ ለዓመታት በቀጠለው ሐይማኖት ተኮር ጥቃት ምክንያት በምስራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ብቻ ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ 17 የሚሆኑት አንድም ሙሉ በሙሉ ፈረሰዋል፣ ወይም እየተካሄደ ባለው የማያባራ ሐይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ ምክንያት አገልግሎት አቁመዋል፡፡ ይህ በአካባቢው የሚፈፀመው ጥቃት ሐይማኖት ተኮር ስለመሆኑ ሁነኛ አስረጅ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ጥቃት ከደረሰባቸው አብያተክርስቲያናት መካከል አኖሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ላሉንጮ አማኑኤል፣ እና ሰንጎ እግዚአብሔር አብ በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ጥቃት ከቅጥር ግቢ እስከ ቤተመቅደስ የፈራረሱና ከጥቅም ውጪ የሆኑ አብያተክርስቲያናት መሆናቸውን ዞብል ፖስት ያገኘው መረጃ ያሳያል።
አክራሪ ታጣቂዎች በደቀኑት ከፍተኛ ስጋት ምክንያት በአሁኑ ወቅት አገልግሎት ያቆሙት ደግሞ ጮጫ እግዚአብሔር አብ፣ ጪሳ ተክለሃይማኖት፣ ጎሮ ሥላሴ፣ ሄላ ሴሮ ማርያም፣ ዘምባባ አርሴማ፣ ዲገሉ መድኅንዓለም፣ ኮኔ እግዚአብሔር አብ፣ ሚታና ዮሐንስ፣ ባቦ ማርያም፣ ሰቄ ገብርሄል፣ጠሬታ በዓለ ወልድ፣ ሽፎ ተክለሃይማኖት፣ ያያ ዮሐንስ፣ ሸንኮራ ቀርሳ ጊዮርጊስ ይገኙበታል።
ራሱን በይፋ ያልገለጠው የአልሸባብ ክንፍ በኢትዮጵያ ስለመኖሩ!
በተለያዩ ጊዜያት በአርሲና አካባቢው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሐይማኖት አባቶች እና አማኞች ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ አካላት ማንነት ሲጠየቅ በመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች ተቋማት በኩል አንዳንድ ጊዜ “ኦነግ ሸኔ” ሌላ ጊዜ “በአካባቢዎቹ አልፎ አልፎ የሚንቀሳቀሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች” የሚሉ ምላሾች ሲሰጡ ይደመጣል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአካባቢው ተደጋግሞ ስለሚፈፀመው ሐይማኖት ተኮር ጥቃት ይህ ነው ሊባል የሚችል አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጥ ባንመለከትም፣ ስለ ጥቃቱ እንዲሁም ጥቃቱን የሚፈፅሙ ታጣቂዎች በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ስለመሆናቸው መንግሥት በቂ መረጃ እንዳለው ዞብል ፖስት ካነጋገራቸው የቃለመጠይቁ ተሳታፊዎች ባገኘው ምላሽ አረጋግጧል።
ለምሳሌ ያህልም፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ሆነው በተሾሙበት ወቅት በአርሲ እና ባሌ አካባቢዎች የአልሸባብ ሰንሰለት መኖሩን የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳውቋል። ይሄንኑ መረጃ በአሁኑ ወቅት የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በጀርመን ሀገር በመከታተል ላይ የሚገኙ አንድ በአፍሪካ ቀንድ የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የአሜሪካን መንግሥት ጨምሮ ከውጭ መንግሥታት ጋር በአማካሪነት እና በተመራማሪነት ይሰሩ የነበሩ ባለሙያ ለዞብል ፖስት አጋርተዋል።
አቶ ተመስገን የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሹም የሆኑበት ጊዜ ማለት ደግሞ የፌዴራል መንግሥቱ ከህወሓት ጋር በጦርነት ላይ የነበረበትን ወቅት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በፈረንጆቹ ነሐሴ 2022 ዓ.ም አልሸባብ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቶ ጥቃት የፈፀመበት ጊዜ ማለት ነው። የአልሸባብን ጥቃት ተከትሎ Voice of America የኢትዮጵያን እና ሶማሊያን የፀጥታ ባለሥልጣናት አነጋግሮ ባወጣው ዘገባ የአልሸባብ ታጣቂዎች ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን በሚያዋስኑ “ሂራን” እና “ባኮል” ተብለው በሚጠሩ የድንበር አካባቢዎች አቋርጠው 150 ኪሎሜትር ያህል የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው መግባታቸው ተመላክቷል።
እኒሁ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በሀገረ ጀርመን በመከታተል ላይ የሚገኙት የቃለመጠይቁ ተሳታፊ አልሸባብ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ መግባቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት አፀፋዊ እርምጃ ከተገደሉት የሽብር ቡድኑ አባላት መካከል በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት በማስታወስ፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሹም በነበሩበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ከእሳቸው በፊትም ሆነ በኋላ አልሸባብ በኢትዮጵያ ሰንሰለት መዘርጋቱን ለደኅንነት መሥሪያ ቤቱ እና ለሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተመሳሳይ መረጃ ይደርሳቸው እንደነበር አያይዘው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የአክራሪ ታጣቂ ቡድኖች ሁኔታ በተመለከተ ከውጭ ተቋማት ሊደርሰው ከሚችለው መረጃ በተጨማሪ በራሱ የመረጃ እና ደኅንነት አሰራር ሊደርስበት የሚችል ጉዳይ እንደሆነ የሚጠበቅ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን በአርሲ እና አካባቢው በክርስቲያኖች ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ ጥቃት ከማስቆም ይልቅ በዝምታ መመልከትን መምረጡን ራሱ መንግሥት ከሚያሳየው ባህሪ መገንዘብ ይቻላል።
በርግጥ ዞብል ፖስት ያደረገው የምርመራ ዘገባ የሚመለከተው በኢትዮጵያ የተዘረጋውን የአልሸባብ ሰንሰለት የተመለከተ ቢሆንም፣ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት 82 የሚጠጉ ለሽብር ተልዕኮ የተመለመሉ የአይኤስ አይኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና ሌሎች በቁጥጥር ስር ባልዋሉት ላይ ተጨማሪ አሰሳ እያደረግኩ ነው ማለቱ ይታወሳል።
ይህ መንግሥት ለሕዝብ ይፋ ያደረገው መረጃ የሚያመላክተው ዓለምአቀፍ እና ቀጠናዊ የሽብር ቡድኖች በኢትዮጵያ አባላትን ከመመልመል ጀምሮ የጥቃት ተልዕኮ እስከመስጠት የደረሰ ሰንሰለት መዘርጋት መቻላቸውን ነው። በክርስቲያኖች ላይ የማያባራ ጥቃት ከሚፈፀምባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የአርሲ ዞንም የእነዚሁ የሽብር ቡድኖች ፍላጎት ማስፈፀሚያ ስለመሆኑ ለዚህ የምርመራ ዘገባ ተጨባጭ መረጃ ካቀረቡት የቃለመጠይቅ ተሳታፊዎች የተገኘው ምላሽ ያሳያል።
የአክራሪ ታጣቂዎች ወታደራዊ ስልጠና እና ርዕዮተ-ዓለማዊ አስተምህሮ በኢትዮጵያ!
ዞብል ፖስት ያነጋገራቸው ሌላኛው የቃለመጠይቁ ተሳታፊ በአሁኑ ወቅት ኑሯቸውን በአሜሪካን ሀገር ያደረጉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ባልደረባ የነበሩ ሲሆኑ፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጉና፣ ሽርካ፣ እና ሆሎንቆ ዋቢ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ያለው አክራሪ ታጣቂ ቡድን ስለመኖሩ እሳቸው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ባልደረባ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት መረጃው እንደነበረው በማስታወስ፣ በጋለማ ተራራ “ቦረ ልኩ” እንዲሁም በሸርካ ወረዳ አመጃ ገለቤ አካባቢ ልዩ ስሙ “አንጆ” ተብሎ የሚጠራ ሁለት የታጣቂዎች ወታደራዊ ማሰልጠኛ ስፍራዎች እንደሚገኙም አያይዘው አስረድተዋል።
እኒሁ የቀድሞው የደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረባ ጉዳዩን ለዞብል ፖስት ሰፋ አድርገው ያብራሩ ሲሆን፣ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች ወታደራዊ ስልጠና ከሚወስዱበት ስፍራ በተጨማሪ ባሌ ሮቤ ውስጥ “ለርዕዮተ-ዓለም እና ፖለቲካዊ አስተምህሮ መስጫ” ብቻ አገልግሎት በሚሰጥ መስጊድ ውስጥ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ጨምረው ገልጸዋል። በዚህ መስጊድ ውስጥ ከተመረጡ ሰዎች ውጭ ማንኛውም የእስልምና ሐይማኖት ተከታይ መግባት እንደማይችልም የቀድሞው የደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረባ አክለው አስረድተዋል።
ዞብል ፖስትም “ታዲያ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ መረጃ ከነበረው ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ያልቻለው ለምን ነበር?” ሲል ለእኒሁ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን እሳቸውም በጉዳዩ ላይ ውይይት ተደርጎበት እንደነበር በማስታወስ ለምን እርምጃ እንዳልተወሰደ ሁለት ምክንያቶችን አስቀምጠዋል።
የመጀመሪያው ምክንያት የመንግሥት ግምገማ “በሽግግር ወቅት ብዙ ስጋትን ያዘሉ ፍላጎቶች ሊታዩ ቢችሉም በሂደት በራሳቸው ጊዜ ይከስማሉ” የሚል እንደነበረ፣ እንዲሁም በሀገሪቷ ለሚከሰቱ ግጭቶች የተለየ ትኩረት መስጠት በመንግሥት በኩል ቅድሚያ የተሰጠው አቅጣጫ ስለነበር የአክራሪ ቡድኖች እንቅስቃሴ እንደ ዋነኛ ስጋት ሆኖ አለመቅረቡ ሁለተኛው ምክንያት ነበር ሲሉ መጽሔታችን ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ምላሻቸውን የሰጡን ሌላኛው የዞብል ፖስት ቃለመጠየቅ ተሳታፊ ለትምህርት የተመለመሉት ሰዎች “ትምርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለወሰዱት የርዕዮተ-ዓለምና ፖለቲካዊ ስልጠና ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ክርስቲያኖችን አግተው ወስደው በሰይፍ ይገድሏቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል። እኒሁ መጽሔታችን ያነጋገርናቸው ግለሰብ አክለውም፣ በተለያዩ ጊዜያት ሰዎች ከቀያቸው እንዲሁም ለጉዳይ በወጡበት ታግተው እንደሚወሰዱ እና ከተወሰዱ በኋላ መልሰው እንደማይገኙ አያይዘው ገልጸዋል።
ከቀድሞው የኢትዮጵያ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረባ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በአርሲ አካባቢ እንዳለው አይነት እንቅስቃሴ ጠንካራ ሊባል ባይችልም ቡድኑ በሐረርጌ “መኤሶ” አካባቢ እንዲሁም በጭሮ ወረዳ “ላሎ ጉዶ” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የተዘረጋ ሰንሰለት እንዳለው ጭምር በመጥቀስ፣ አክራሪ ታጣቂዎችበአካባቢዎቹ አልፎ አልፎ ግድያን ጨምሮ ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶችን እንደሚፈፀሙ ጨምረው ገልፀዋል።
ከኢትዮጵያ ሶማሊያ ያለው የግንኙነት መስመር!
መጽሔታችን ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው አካላት ጋር ቃለምልልስ አድርጎ ያገኘው ምላሽ እንደሚያሳየው ራሱን የዚህ ቡድን ክንፍ ነኝ ብሎ በይፋ ባይገለፅም ከአልሸባብ ጋር የተዘረጋ ሰንሰለት ያለው ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ባሌ አካባቢዎች መኖሩን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ መረጃዎችን አግኝቷል።
ይሄንን ተከትሎ በአካባቢዎቹ ያለው አክራሪ ታጣቂ ቡድን እና አልሸባብ “ያላቸው ግንኙነት አድማሱ እስከምን ድረስ የሰፋ ነው?” የሚለውን ጉዳይ ለማወቅ ከዚህ ቀደም በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሥሪያ ቤት ሠራተኛ የነበሩ እና በአሁኑ ሰዓት ትኩረቱን በምስራቅ አፍሪካ የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ አድርጎ የሚሰራ ተቀማጭነቱ በኬኒያ ናይሮቢ በሆነ የጥናትና ምርምርና ተቋም ውስጥ በተመራማሪነት የሚሰሩ የተቋሙን ባልደረባ ዞብል ፖስት ለዚህ የምርመራ ዘገባ አግኝቶ የማነጋገር ዕድል ያገኘ ሲሆን፣ ከእኒሁ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ ተጨባጭ መረጃዎችን ማግኘት ተችሏል ።
መጽሔታችን ከእኒህ የምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ተመራማሪ ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያውያን አልሸባብን በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ይቀላቀላሉ። በኢትዮጵያ ያሉ የሀገር ውስጥ የግንኙነት መስመሮችን በመጠቀም በዶሎ፣ ጅግጅጋ፣ እና በሽንሌ በኩል በድንበር በማቋረጥ አልሸባብን መቀላቀል አንደኛው መንገድ መሆኑን መጽሔታችን ያገኘው መረጃ ያሳያል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሰኔ 2013 ዓ.ም በአርሲ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ክርስቲያኖች እና የአማራ ተወላጆች የተገደሉበትን ክስተት ያስተባበሩና የመሩ ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ሻሸመኔ ከሚገኝ እስር ቤት እንዲያመልጡ ተደርጎ ወደ ሶማሊያ እንዲሄዱ መደረጋቸውን ሌላኛው የመጽሔታችን ቃለምልልስ ተሳታፊ አስረድተዋል።
ከእስር አምልጠው ወደ ሶማሊያ የሄዱት ሰዎች 4 ሲሆኑ፣ ሁኔታው በሀገር ውስጥ ያለው የአልሸባብ የግንኙነት መስመር ኢትዮጵያውያን ወደ ሶማሊያ ተጉዘው ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ያደርጋል የሚለውን ጉዳይ የሚያጠናክር ነው። ከዚህም በተጨማሪ፣ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ያላቸው አክራሪ ቡድኖች የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ጨምሮ ሌሎች ሀገራዊ ቀውሶች በሚከሰቱበት ጊዜ መሰል ሁኔታዎችን ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶችን ለመፈፀም እንደ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚጠቀሙባቸው መረዳት ይቻላል።
ሁለተኛው ኢትዮጵያውያን አልሸባብን የሚቀላቀሉበት መንገድ ደግሞ በስደተኛ ጣቢያዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መልምሎ በመውሰድ ወደ ቡድኑ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ Sky News በልዩ ዘጋቢዋ Alex Crawford አዘጋጅነት ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ነሐሴ 2025 ዓ.ም ለዕይታ ባቀረበው “Hunting for ISIS: A Warning from Africa” በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ ልክ እንደ አልሸባብ ሁሉ ኢትዮጵያውያን አይኤስ አይኤስን ከስደተኛ ጣቢያዎች በመውጣት እንደሚቀላቀሉ የፑንትላንድ ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ መዘገቡ አይዘነጋም።
ከቀድሞው የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሥሪያ ቤት ከአሁኑ ተቀማጭነቱን በኬኒያ ካደረገው የምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች የጥናትና ምርምር ተቋም ባልደረባ ያገኘነው ተጨማሪ ምላሽ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያውያን በሶማሊያ የሚገኘውን አልሸባብ ከመቀላቀል ባሻገር ከሶማሊያ ስልጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው እንደሚገቡ፣ እንዲሁም የሶማሊያ መንግሥት የገጠመው ውስጣዊ የፀጥታ ችግር እና የፀጥታ ተቋማቱ መዳከም ለዚህ ሁኔታ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አያይዘው አብራርተዋል። ይሄንን ጉዳይ አስመልክቶም የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት የድንበር ላይ ቁጥጥሮችን በማጠናከር ዙሪያ ያተኮሩ ተደጋጋሚ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገው እንደሚያውቁ አክለው አስረድተዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ፣ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች የወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እና ርዕዮተ-ዓለማዊ ስልጠና በሚወስዱባቸው የአርሲና ባሌ ሮቤ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ (ምላሽ በሰጡን ግለሰብ አገላለፅ የአረብ እና ሶማሌ የፊት ገፅታ ያላቸው) ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲንቀሳቀሱ እንደሚታዩ መጽሔታችን ያነጋገራቸው በአሁኑ ሰዓት ነዋሪነታቸውን በሀገረ አሜሪካ ያደረጉት የቀድሞው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ባልደረባ አስረድተዋል።
እንደ እሳቸው መረዳት እና ምላሽ፣ የደኅንነት መስሪያ ቤቱ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ባይሰጠውም፣ “እነዚህ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ሰዎች ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች በተደጋጋሚ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት ለታጣቂዎቹ ስልጠና (የርዕዮተ-ዓለምና ፖለቲካዊ አስተምህሮት) ለመስጠት ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ከዚህ የዞብል ፖስት የምርመራ ዘገባ ከተገኘው ምላሽ ጋር በሚመሳሰል መልኩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባሳለፍነው ሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ለሽብር ተልዕኮ የተመለመሉ 82 የአይኤስ አየኤስ አባላትን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ፣ አዳማ፣ ሃሮማያ፣ ሻሸመኔ፣ ባሌ፣ጅማና ሻኪሶ ከተማ ዙሪያ እንዲሁም በአማራ ክልል ከሚሴ አካባቢ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞንና ሃላባ ቁሊቶ ከተማ፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማና በሐረሪ ክልል በቁጥጥር አውያለሁ ማለቱ አይዘነጋም።
ይህ ሁኔታ በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የሚገኙ የሽብር ቡድኖችን የሚቀላቀሉ ኢትዮጵያውያን የሁለቱን ሀገራት ድንበር የመግቢያ እና መውጫ በር እንዳደረጉት ያሳያል። ይህም የኢትዮጵያንና ሶማሊያን ድንበር የሽብርተኛ ቡድኖች ለመሸጋገሪያነት የሚጠቀሙበት ሁነኛ የመተላለፊያ መስመር ያደርገዋል።
ከላይ በአርሲና ባሌ አጎራባች አካባቢዎች ስለመኖሩ በጠቀስነው የአክራሪ ታጣቂዎች የአስተምህሮ ስፍራ የውጭ ሀገራት ሰዎች ሳይቀር የመታየታቸው ሁኔታ የሚነግረንን መረጃ ተንተርሰን፣ እንዲሁም ከሶማሊያ ስልጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ የአልሸባብ አባላትን፣ ወይም የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳሳወቀው በሶማሊያ ከሚገኘው አይኤስ አይኤስ ተልዕኮ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሰዎችን ሁኔታ ስንመለከት፣ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ሰዎች በኢትዮጵያና ሶማሊያ የድንበር አካባቢዎች አቋርጠው በመምጣት በኢትዮጵያ ለዘረጉት ኢስላማዊ ታጣቂ ቡድን ሰንሰለት አንድም ወታደራዊ ሌላም የርዕዮተ-ዓለማዊ አስተምህሮ ይሰጣሉ ወደሚለው መደምደሚያ ይወስደናል።
ይህ የሁኔታዎች ትስስር የሚነግረን አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ እንደ አልሸባብ ያሉ ኢስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ለተልዕኳቸው አስቻይ የሆኑ የግንኙነት መስመሮችን በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የቡድኑን ርዕዮተ-ዓለም ተኮር ሐይማኖታዊ ፍላጎት ከሚደግፉ አካላት ጋር በመቀናጀት የግንኙነት ሰንሰለት መዘርጋት መቻላቸውን ነው። በዚህ የምርመራ ዘገባ የተገኙ ውጤቶችም በአርሲ እና አካባቢው የሚፈፀሙ የማያባሩ ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶችን እንደ አይን ገላጭ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።
ራሳቸውን ዓለምአቀፋዊ እና ርዕዮተ-ዓለም ተኮር ታጣቂ ቡድን አድርገው የሚገልፁ ኃይሎች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተፅዕኖ አድማስቸውን (Sphere of Influence) ማስፋት አንደኛው ስትራቴጂያቸው ነው። ኢትዮጵያን “ዘላለማዊ ጠላቴ ናት” የሚለው እና በምስራቅ አፍሪካ ሶማሌዎች የሚገኙባቸውን ግዛቶች ጠቅልሎ “ኢስላማዊ መንግሥት” ለማቋቋም የሚንቀሳቀሰው አልሸባብም ሆነ አይኤስ አይኤስ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፅዕኖ አድማሳቸውን ማስፋት ዋነኛ ትኩረታቸው ስለመሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ።
በአርሲና በሌሎች አካባቢዎች በክርስቲያኖች ላይ የሚፈፀሙ ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶችም እነዚሁ ኢስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ሊያስፋፉት የሚፈልጉት ርዕዮተ-ዓለማዊ ፍላጎት አካል ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ በዚህ የምርመራ ዘገባ የተገኙ ውጤቶች ያሳያሉ።
“መጪው ጊዜ ምን ሊመስል ይችላል?” እንደ መደምደሚያ!
በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅን እና የሀገር ሉዓላዊነትን የማስከበርን ትንሹን ሚና መወጣት ባለመቻሉ በሀገሪቷ ብሔራዊ ስጋት ሆነው ከሚቀጥሉ ሀገራዊ ቀውሶች መካከል “ሐይማኖት ተኮር ጥቃት” አንዱ ስለመሆኑ በርካታ ተጨባጭ ማሳያዎች አሉ። ይህ ሁኔታ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ የተጣመሩ አክራሪ ቡድኖች አስተሳሰብ እንዲስፋፋ እና የጥፋት ፍላጎቶቻቸው እንዲፈፀሙ ምቹ መደላድልን ሊፈጥር ይችላል።
እንደ አልሸባብ ያሉ የሽብር ቡድኖችን አስተምህሮ እና ፖለቲካዊ ፍላጎት ሰፋ አድርገን ስንመለከት ደግሞ፣ በሀገር ቤት የተከሉትን የግንኙነት መስመር በመጠቀም ሐይማኖት ተኮር ጥቃቶችን ከመፈፀም ባሻገር በመካከለኛው ምስራቅ እና አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት እንደተመለከትነው በኢትዮጵያም ከከፍተኛ ሀገራዊ ውድመት እስከ ሀገር ፍርሰት ሊያስከትሉ የሚችሉ ውጥኖች ሊኖሯቸው እንደሚችል በአፍሪካ ቀንድ ካላቸው ይዞታ እና በቀጠናው ላይ ከሚያሰራጩት ፕሮፓጋንዳ መረዳት ይቻላል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በሱዳን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት የግንኙነት መሻከር፣ እንዲሁም ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ተፅዕኖ እያደገ መምጣቱ፣ ኢትዮጵያን ለአክራሪ ቡድኖች የመስፋፋት እንቅስቃሴ እና ለሌሎች አሉታዊ የውጫ ፍላጎቶች ይበልጥ ተጋላጭ እንድትሆን የሚያደርጉ የወቅቱ ቀጠናዊ ትኩሳቶች ናቸው።


