መቀመጫውን በለንደን ያደረገው የእንግሊዙ እውቁ “The Economist” መፅሔት፣ ከሁለት ወራት በፊት በፈረንጆቹ መጋቢት 31፣ 2025 ዓ.ም በጎጃም ሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ በብራቃት ከተማ በበርካታ ንፁሃን ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ “የዐቢይ አህመዷን አስከፊ ኢትዮጵያ የሚገልፅ ጭፍጨፋ” በሚል አርዕስት በዛሬው ዕለት ባወጣው አስደንጋጭ ዘገባ አስነብቧል።
መፅሔቱ ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ “በትንሿ ብራቃት ከተማ በፋኖ እና በዐቢይ አህመድ ሠራዊት መካከል ለአምስት ሰዓታት ያህል ውጊያ ከተደረገ በኋላ፣ የአገዛዙ ወታደሮች ወደ ከተማዋ ዘልቀው መግባት የቻሉ ሲሆን፣ ወደ ከተማ እንደገቡ ወዲያውኑ ንፁሃንን ከቤታቸው እየጎተቱ በማውጣት መግደል ጀመሩ” በማለት ሶስት የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
The Economist በዘገባው፣ የአገዛዙ ሠራዊት ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ከአራት እስከ ስድስት የሚሆኑ ወታደሮች በቡድን በቡድን እየሆኑ ንፁሃንን ቤት ለቤት እየጎተቱ በማውጣት መንገድ ላይ እጃቸውን ወደኋላ አስድርገው በማንበርከክ አስከፊ የሚባል ጭፍጨፋ መፈፀማቸውን ይገልፃል።
ሁነቱን ተደብቆ ሲከታተል የነበረ አንድ የአይን እማኝ፣ “አራት ሴቶች በከተማዋ የአውቶብስ መናሃሪያ አጠገብ እጃቸውን ወደኋላ አድርገው እንዲንበረከኩ ከተደረጉ በኋላ፣ ወታደሮቹ ከጀርባ ቆመው በደገኑትን መሳሪያ አውቶማቲክ ተኩሰው ገደሏቸው” በማለት በወቅቱ የነበረውን አስደንጋጭ ሁኔታ ለ The Economist ያስረዳል። ይሄው የአይን እማኝ፣ አንድ ካህን ከቤተክርስቲያን አጠገብ በወታደሮች መገደላቸውን ጭምር እንደተመለከተ መፅሔቱ በዘገባው ያስረዳል።
ግድያው በተፈፀመው ማግስት ጠዋት፣ ወደ ብራቃት ከተማ የተመለሰ ሌላ የአይን እማኝ፣ “ሬሳዎች በየቦታው ወድቀው ማየቱን እና በቦታው 56 አስከሬኖችን እንደቆጠረ” The Economist ባስነበበው ዘገባ ተመላክቷል።
ዘገባው አያይዞ፣ “የአገዛዙ ወታደሮች በፋኖ ሽንፈት በሚያጋጥማቸው ወቅት፣ ሽንፈታቸውን ለማካካስ በንፁሃን ላይ የጅምላ ግድያን በመፈጸም፣ በርካታ ንፁሃንን ያለጥፋታቸው የበቀል ማወራረጃ ያደርጋሉ” በማለት ገልጿል።


