ሰኔ 23/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
የፌዴራል ፖሊስ በሠራዊት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየተመናመነ እንደሆነ ተቋሙ በቅርቡ ባደረገው ግምገማ ላይ መግለፁን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
የመረጃ ምንጫችን እንዳስረዱት፣ ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት አባላት ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በጦርነት ግንባር እንዲሳተፉ መደረጋቸው ተቋሙ ለገጠመው የሰው ኃይል መመናመን ዋነኛው ምክንያት ነው ተብሏል።
ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከተቆናጠጠ ወዲህ በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት ሊባል በሚችል መልኩ ተከታታይ ጦርነቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ የፌዴራል ፖሊስ ልክ እንደ መከላከያ ሠራዊቱ ሁሉ በጦርነት እንዲሳተፍ ግዳጅ ተጥሎበታል። ይህ ሁኔታ ሠራዊቱ በቁጥር እንዲመናመን ካደረጉት ምክንያቶች ዋነኛው መሆኑን መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱ አንድ የሠራዊቱ አባል አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የፌዴራል ፖሊስ መዋቅር ከኮሚሽነር ጄኔራል ደምመላሽ ገብረሚካኤል እስከ ሌሎች ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች በአንድ ብሔር ቁጥጥር ስር በመሆናቸው ምክንያት ኦሮሞ ያልሆኑ በርካታ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከሠራዊቱ እየከዱ እንደሚወጡ በመጠቆም፣ ሁኔታው ተቋሙ በሰው ኃይል ቁጥር እየተመናመነ ለመምጣቱ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለመፅሔታችን አስረድተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ሁለት ዓመታትን በደፈነው በአማራ ህዝብ ላይ የታወጀው ጦርነት ሠራዊቱ ለገጠመው የሰው ኃይል መመናመን ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ፣ የፌዴራል ፖሊስ ያደረገው ግምገማ እንደሚጠቁም የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።
ለአብነት ያህልም፣ ወደ አማራ ክልል ለግዳጅ የተላኩ የፌዴራል ፖሊስ አባል የነበሩ በርካታ የአማራ ተወላጆች በአማራ ክልል የተለያዩ ክፍለሀገሮች የሚገኙ የፋኖ አደረጃጀቶች እንደተቀላቀሉ የተቋሙን ግምገማ አስመልክቶ መረጃ ያደረሱን የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጭ አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ በርካታ የፌዴራል ፖሊስ አባል የነበሩ የአማራ ተወላጆች “ፋኖን ትደግፋላችሁ” እንዲሁም “ለፋኖ መረጃ ታቀብላላችሁ” እየተባሉ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ወታደራዊ እና ድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ መታሰራቸውን ከፌዴራል ፖሊስ አባላት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በቴክኖሎጂ እና በተሽከርካሪ ግብዓቶች ተቋሙን አዘመኛለሁ ማለቱ የሚታወስ ቢሆንም፣ በሰው ኃይል ረገድ ግን “የሠራዊት ቁጥራችን በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኗል” ሲል ተቋሙ በቅርቡ ባደረገው አጠቃላይ ግምገማ ገልጿል።
የፌዴራል ፖሊስ የገጠመውን የሠራዊት መመናመን ተከትሎ፣ በኑሮ ውድነት ጫና እና በሌሎች አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ምክንያት በአዲስአበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ሕዝባዊ አመፅ ሊከሰት ይችላል በሚል፣ አዳዲስ ሰልጣኞች በአስቸኳይ እንዲመለመሉ እና በሰው ኃይል የተመናመነው ተቋም መልሶ እንዲጠናከር ጠቅላይ ሚንስትሩ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።


