ሰኔ 24/2017 ዓ.ም—ዞብል ፖስት ዜና!
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ዘጠኝ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አፍነው መውሰዳቸውን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ታጣቂዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አፍነው የወሰዱት በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉት ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ሰበታ፣ እና ጫንጮ አካባቢዎች እንደሆነ መረጃውን ለመፅሔታችን ያጋሩት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቅሰዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኦነግ ሠራዊት አመራር የነበረው ጃል ሰኚ ለመንግሥት እጅ ከሰጠ በኋላ “ዘመቻ ፅናት” የሚል ወታደራዊ ዘመቻ በኦነግ መታወጁ የሚታወስ ሲሆን፣ የቡድኑ ታጣቂዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች እና በኦሮሚያ ክልል ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ጦርነት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ከቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ሰበታ፣ እና ጫንጮ አካባቢዎች በኦነግ ታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት፣ ቡድኑ ዘመቻ ፅናትን ካወጀበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያጋሩት ምንጫችን አያይዘው ገልጸዋል።
የመረጃ ምንጫችን አክለውም፣ በአዲስአበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች አመራር የነበሩት ዘጠኙ የወረዳ ባለሥልጣናት ታፍነው የተወሰዱት በተለያዩ ጊዜያት እንደሆነ እና ከተወሰዱበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ያሉበት ቦታ እንደማይታወቅ ሁኔታውን አስመልከተው ለዞብል ፖስት በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።
መረጃውን ያገሩን ምንጫችን “በኦነግ ታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት ባለሥልጣናት በህይወት ይኑሩ ወይም አይኑሩ የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ ባለሥልጣናቱ ታፍነው ከተወሰዱበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሁኔታ አያይዘው ለመፅሔታችን አስረድተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ከ253 በላይ የወረዳ ባለሥልጣናት በኦነግ ታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸውን እና አብዛኛዎቹ ደብዛቸው መጥፋቱን ለመፅሔታችን መረጃውን ያደረሱት ምንጮች የክልሉን አጠቃላይ ሁኔታ አያይዘው አስረድተዋል።


