ሰኔ 25/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የትግል እንቅስቃሴ የጀመረው የኤርትራው የተቃውሞ ንቅናቄ ብርጌድ ንሓመዱ በጋራ ለመስራት ውይይት መጀመራቸውን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
በትግራይ ፖለቲካ ህወሓትን ለመተካት አቅዶ በቀድሞ የህወሓት አመራሮችና አባላት የተመሰረተው ስምረት ፓርቲ እና የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመጣል የሚታገለው ብርጌድ ንሓመዱ፣ በፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ከሰሞኑ ንግግር መጀመራቸውን የመፅሔታችን የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
ስምረት ፓርቲ እና ብርጌድ ንሓመዱ በጋራ ለመስራት የጀመሩትን ውይይት ያመቻቹት የመከላከያ ሠራዊቱ ወታደራዊ ደኅንነት ኃላፊ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና ሲሆኑ፣ ጄኔራሉ የሁለቱን ኃይሎች ተወካዮች በአካል አግኝተው እንዳነጋገሩ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንዳስቀመጡ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከሚመራው ህወሓት እና ከኤርትራ የተውጣጡ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎች፣ “ፅምዶ” የተሰኘ ጥምረት መፍጠራቸውን እና ተከታታይ ውይይቶችን ማካሄዳቸውን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ።
የትግራዩ ስምረት ፓርቲ እና የኤርትራው ብርጌድ ንሓመዱ በጋራ ለመስራት ውይይት የጀመሩት፣ ፅምዶ ለተሰኘው የህወሓት እና የኤርትራ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጥምረት አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ መሆኑን መረጃውን ያደረሱን ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።
የኤርትራው የተቃውሞ ንቅናቄ ብርጌድ ንሓመዱ በዐቢይ አህመድ መንግሥት የሚደገፍ ሲሆን፣ ቡድኑ በቅድሚያ በአዲስአበባ ቢሮ እንዲከፍት ተደርጎ የነበረ ሲሆን በመቀጠልም በኢትዮጵያ አፋር ክልል መጋሊ ቀጠና የትጥቅ ትግል ለማድረግ ወታደራዊ ስልጠና መጀመሩን፣ ዞብል ፖስት ቀደም ብሎ መዘገቡ ይታወሳል።
የብርጌድ ንሓመዱ የዲፕሎማሲ ክንፍ ኃላፊው አቶ በየነ ገብረእግዚአብሔር “የኢሳያስ አፈወርቂን መንግሥት ለመጣል ለሚያደርጉት ትግል የዐቢይ አህመድ መንግሥት የድርሻውን የሚወጣ ከሆነ፣ የኢትዮጵያን የባህር በር እና ተያያዥ ጥያቄዎችን እኛ ልንመልስላቸው እንችላለን” ሲሉ ለቢቢሲ የአማርኛው ዜና ክፍል ባለፈው ሚያዚያ ወር ገልጸው ነበር።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የስምረት ፓርቲ ወታደራዊ ክንፍ እንደሆነ የሚነገርለት እና በደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራውን ህወሓት ለመጣል ከህወሓት የወጡ ወታደራዊ መሪዎች እና ታጣቂዎች ያደራጁት እና በቅርቡ “የትግራይ ሠላማዊ ኃይል” የሚል ስም የተሰጠው ቡድን፣ በቅርቡ የትጥቅ ትግል መጀመሩን በይፋ ማሳወቁ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የኃይል አሰላለፍ ለውጦች እየተከሰቱ ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች አንዳቸው የሌላኛውን የተቃዋሚ ኃይል የመደገፍ እና የማስታጠቅ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው ገሃድ በመውጣት ላይ ይገኛል።
በኤርትራ በኩል ከህወሓት ጋር ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥምረት የመፍጠር ሂደት ውስጥ የተገባ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ከፈጠረው ህወሓት በተቃራኒ የቆሙ የትግራይ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ኃይሎችን እና የኤርትራውን ብርጌድ ንሓመዱ በመደገፍ ላይ ይገኛል።
ሁኔታው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለውን ውጥረት ወደበለጠ መካረር ከፍ እንደሚያደርገው የብዙዎች ስጋት ሲሆን፣ ይሄንን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል እና ቀድሞውንም በግጭት እና ውጥረት በሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ፖለቲካ አስከፊ ቀውስን ሊያስከትል የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው ተብሎ ይገመታል።


