Wednesday, May 6, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየኢትዮጵያ መንግሥት በኬኒያ የሚንቀሳቀሱ የኦብነግ አመራሮች ተላልፈው እንዲሰጡት ለኬኒያ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡ...

የኢትዮጵያ መንግሥት በኬኒያ የሚንቀሳቀሱ የኦብነግ አመራሮች ተላልፈው እንዲሰጡት ለኬኒያ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡ ተነገረ።

ሰኔ 26/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!

የዐቢይ አህመድ መንግሥት በኬኒያ ናይሮቢ የሚንቀሳቀሱ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ፖለቲካዊ አመራሮች ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ ለኬኒያ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።

ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው ኦብነግ፣ ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከመንግሥት ጋር የሠላም ስምምነት ተፈራርሞ ሠላማዊ ትግል ለማድረግ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ፓርቲው በገጠመው ውስጣዊ መሰንጠቅ ምክንያት፣ የኦብነግ ሊቀመንበር የነበሩት አብዲራህማን ማህዲ የራሳቸውን ቡድን ይዘው በሶማሊያ መካከለኛው ሸበሌ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ዞብል ፖስት መዘገቡ የሚታወስ ነው።

ኦብነግ ከስድስት ዓመታት በፊት በኤርትራ አሥመራ የኦብነግ ታጣቂዎችን ወደ ክልሉ የፀጥታ ኃይል ማስገባት፣ በጦርነት የተጎዱትን መልሶ ማቋቋም፣ የኦጋዴንን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ መመለስ እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከመንግሥት ጋር መፈራረሙ የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጅ፣ “የዐቢይ አህመድ መንግሥት ቃሉን አጥፎ ያደረግናቸው ስምምነቶች እንዳይፈፀሙ አድርጓል” እንዲሁም “የሶማሌ ክልል መንግሥት ፓርቲውን ለማዳከም እየሰራ ነው” በሚል በአብዲራህማን ማህዲ የሚመራው የኦብነግ ክንፍ በሶማሊያ የትጥቅ ትግል ለማድረግ መወሰኑን በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ።

አብዲራህማን የሚመሩት የኦብነግ ክንፍ ከሠላም ስምምነቱ በኋላ በኢትዮጵያ ያደርግ የነበረውን ሠላማዊ ትግል ማቆሙንና ራሱን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ማግለሉን ተከትሎ፣ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ለአዲስ ትግል እያደራጀ እንደሆነ ያስታወቀው በካቲት 23/2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነበር።

በሠላማዊ ትግል ለመቀጠል የወሰነው እና የትጥቅ ትግል ለማድረግ በወሰነው ቡድን ከፍተኛ ወቀሳ የሚቀርብበት የኦብነግ ሌላኛው ክንፍ በበኩሉ፣ በሚያዚያ 1/2017 ዓ.ም ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ጉባኤው አብዲራህማን ማህዲን ከሊቀመንበርነት አንስቶ በሌላ መተካቱ ይታወሳል።

ኦብነግ በኬኒያ የሚኖሩ በርካታ ደጋፊዎች እና አባላት ያሉት ሲሆን፣ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ የድርጅቱ አመራሮች እና አባላት የሚሳተፉበት የድርጅቱ ጉባኤ እና የከፍተኛ የአመራሮቹ ምስጢራዊ ስብሰባ የሚደረጉት በኬኒያ እንደሆነ በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኦብነግ አመራሮች ተላልፈው እንዲሰጡት ከመጠየቁ ጋር ተያይዞ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ከኬኒያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ከጥቂት ወራት በፊት በናይሮቢ ተገናኝተው “ሽብርተኝነትን እና የተደራጁ ወንጀሎች በጋራ መከላከል” በሚሉ ጉዳዮች ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱማሌ ክልል ርዕስመስተዳድር ሙስጠፊ መሐመድ ባሳለፍነው ወር ወደ ኬኒያ ተጉዘው የነበረ ሲሆን፣ ከቢቢሲ የአማርኛው ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ኦብነግ የትጥቅ ትግል የመጀመር አዝማሚያ እያሳየ እንደሆነ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

የመፅሔታችን የመረጃ ምንጭ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ባሳለፍነው ጥር ወር አጋማሽ በናይሮቢ ተገናኝተው ሽብርተኝነትን እና የተደራጁ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል መስማማታቸውን በማስታወስ፣ በኬኒያ የሚንቀሳቀሱ የኦብነግ የፖለቲካ አመራሮች ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ ኢትዮጵያ ለኬኒያ መንግሥት ጥያቄ አቅርባለች ሲሉ ለዞብል ፖስት አብራርተዋል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች