Friday, May 8, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየኢትዮጵያ አማፂ ቡድኖች ማዘዣ ጣቢያቸውን በሱዳን እየከፈቱ ነው።

የኢትዮጵያ አማፂ ቡድኖች ማዘዣ ጣቢያቸውን በሱዳን እየከፈቱ ነው።

ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ታጠቁ ቡድኖች እንደ ማዘዣ ጣቢያ ሆነው የሚያገለግሉ ቢሮዎችን በሱዳን እየከፈቱ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።

ታጣቂ ቡድኖቹ በሱዳን የየራሳቸውን ቢሮ መክፈታቸው የተነገረ ሲሆን፣ በሀገሪቱ እየተደረገ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ከሁለቱ ተፈላሚ ኃይሎች ለጄኔራል አልቡርሃን ወግኖ የሚዋጋውን አርሚ 70 የተባለውን ኃይል ያሰለፈው ህወሓት ቢሮውን የከፈተው ከሌሎች ቀደም ብሎ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የህወሓቱ ጄኔራል ፍስሃ ኪዳኑ በቅርቡ ከትግራይ ወደ ሱዳን ተጉዞ የታጣቂዎችን ቢሮ መጎብኘቱን እና ከግብፅ እና ሱዳን ባለሥልጣናት ጋር የጦር መሳሪያ አቅርቦትን በተመለከተ ውይይት ማድረጉን ዞብል ፖስት ያገኘው መረጃ ያሳያል።   

አርሚ 70 የተሰኘው ኃይል ለረዥም ጊዜ በውትድርና ከቆዩት አባላቱ በተጨማሪ በጥቅምት በ2013 ዓ.ም በማይካድራ ከ1500 በላይ የአማራ ተወላጆች ላይ የቤት ለቤት ጭፍጨፋ ከፈፀመ በኋላ ወደ ሱዳን የሸሸውን “የሳምሪ ቡድን” እንደሚያካትት በርካታ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን፣ አርሚ 70 ወልቃይትን በኃይል ለመቆጠጣር በሱዳን የተቀመጠ ኃይል እንደሆነ በርካቶች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይደመጣል።

ሌላኛው በሱዳን ቢሮ የከፈተው ታጣቂ ኃይል ከዚህ ቀደም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር የሠላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ስምምነቱን አፍርሰው መልሰው ትጥቅ ካነሱ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂዎች የተውጣጣ ኃይል መሆኑ ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ እና የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የሚባሉ ሁለት ታጣቂ ቡድኖች ባሳለፍነው ሰኔ 2016 ዓ.ም ከክልሉ መንግሥት ጋር የሠላም ስምምነት ማድረጋቸው ከተነገረ በኋላ የድርጅቶቹ አንጃዎች መልሰው ትጥቅ በማንሳት ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ውጊያ ማድረጋቸውን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቤንሻንጉል ሕዝብ ነፃ አውጭ ንቅናቄ መሪ የነበረው አብዱልዋህብ መሐድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ ከሚገኝ እስር ቤት፣ ከሦስት ዓመታት በፊት አምልጦ ወደ ሱዳን መግባቱ የሚታወስ ነው።

የንቅናቄው መሪዎች ከእስር ካመለጠ በኋላ ከሱዳን ሆኖ ታጣቂዎችን የመመልመል እና የማደራጀት ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ከዚህ ቀደም የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ በሰራነው ዘገባ መግለፃችን አይዘነጋም።

በሌላ በኩል በሱዳን ብሉናይል ግዛት ወታደራዊ ስልጠና ወስደው የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የገቡ በርካታ ታጣቂዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ እና በዓባይ ግድብ አቅራቢያ ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት መፈፀማቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ ቡድን በሱዳን ቢሮ ከከፈቱት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ባይታወቅም፣ ሁለቱም ኃይሎች የወታደራዊ ቁሳቁስ፣ የስልጠና እና የገንዘብ ድጋፍ ከግብፅ መንግሥት የሚያገኙ ታጣቂ ቡድኖች ናቸው።     

ሌላኛው በሱዳን ቢሮ ከፍቶ እንዲንቀሳቀስ የተደረገው የቅማንት ታጣቂ የሚባለው ቡድን ሲሆን፣ ቡድኑ በሱዳን ቢሮ የከፈተው ከሌሎች ዘግየት ብሎ መሆኑን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።

የቅማንት ታጣቂ ቡድን ከዚህ ቀደም በጎንደር የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት በመፈፀም የሚታወቅ ሲሆን፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ከህወሓት ጋር በመሰረተው ጥብቅ ቁርኝት ከህወሓት የጦር መሳሪያ ድጋፍ፣ የገንዘብ፣ እንዲሁም ወታደራዊ ስልጠና ሲያገኝ መቆየቱን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው ታጣቂ ቡድኖች በሱዳን ቢሮ እንዲከፍቱ የተደረገው በፖርት ሱዳን እና ገዳሪፍ ከተሞች ሲሆን፣ በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የታጣቂ ቡድኖቹ ደጋፊዎች እና ፖለቲካዊ መሪዎች ወደ ሱዳን ተጉዘው ከታጣቂ ቡድኖቹ አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

የግብፅ መንግሥት በበኩሉ በሱዳን ቢሮ ለከፈቱት ታጣቂዎች በገንዘብ፣ በወታደራዊ ቁሳቁስ እና ስልጠና፣ እንዲሁም በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጫችን አብራርተዋል።

ግብፅ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ጄኔራል አልቡርሃንን በመደገፍ የምትታወቅ ሲሆን፣ ጄኔራሉ የሚመሩት የሱዳን ብሔራዊ ጦር በተቆጣጠራቸው የሱዳን ግዛቶች ቢሮ እንዲከፍቱ የተደረጉትን የኢትዮጵያ ታጣቂ ቡድኖች ደግሞ ጎን ለጎን በመደገፍ ትገኛለች።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች