ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የራያ ወሎ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ “በህወሓት ለተፈፀመብን ወረራ የፌዴራል መንግሥቱ ተጠያቂ ነው” ነው ሲል ከሰሞኑ አሳውቋል። ኮሚቴው በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ይህንን ክስ ያቀረበው በሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ ነው።
የህወሓት ታጣቂዎች የራያ አማራ ሕዝብ ታሪካዊ የማንነት እና ወሰን ጥያቄዎች የሚያነሳባቸውን ስድስት ወረዳዎች በኃይል ተቆጣጥረው ከያዙበት ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በሕዝቡ ላይ ግድያ፣ አፈና ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እና ዝርፊያ እየፈፀሙበት እንደሚገኝ ባወጣው መግለጫ ላይ በመግለጽ፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ላለው የተራዘመ ጥቃት አገዛዙን ኃላፊነቱን ይወስዳል ሲል ኮሚቴው በመግለጫው አስታውቋል።
የራያ ወሎ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያወጣው የአቋም መግለጫ ባለ ሠባት ነጥብ ሲሆን፣ በተራ ቁጥር አንድ ላይ “የራያ አማራ ሕዝብ በህወሓት ሁለንተናዊ በደል እየደረሰበት ያለው ህወሓት ስድስቱን የራያ ወረዳዎች በኃይል ሲቆጣጠር የፌዴራል መንግሥቱ ባላየ እና ባልሰማ ሆነ ብሎ በመመልከቱ ነው” ሲል ክስ አቅርቧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ዞብል ፖስት በሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ከህወሓት ወረራ ጊዜ ጀምሮ የአካባቢውን እና ሕዝቡን ሁኔታ አስመልክቶ በሰራው የምርመራ ዘገባ ራያ አላማጣ፣ አላማጣ ከተማ፣ ራያ ኮረም፣ ራያ ኦፍላ፣ ራያ ባላ፣ እና ራያ ዛታ በህወሓት ታጣቂዎች ወረራ ሲፈፀምባቸው በራያ አዘቦ እና ራያ አላማጣ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰፍረው የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ሁኔታውን በዝምታ መመልከታቸውን ማጋለጣችን አይዘነጋም።
ከዚህም በተጨማሪ፣ “የፌዴራል መንግሥት የህወሓት ታጣቂዎች አካባቢውን እንዲቆጣጠሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል የሚል ግምት አልነበረንም” በማለት የተፈፀመባቸውን ወረራ “የዐቢይ አህመድ መንግሥት የፈፀመብን ታላቅ ክህደት” ሲሉ መግለፃቸውን በምርመራ ዘገባው ወቅት ያነጋገርናቸውን የራያ አማራዎች ስሜት አያይዘን ማጋራታችን ይታወሳል።
የራያ ወሎ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አያይዞም የፌዴራል መንግሥቱ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዳይፈፀም እና በስምምነቱ መሠረት የራያ ወሎ አማራ መራር ትግል ያደረገበት የማንነት እና ወሰን ጥያቄ በዘላቂነት እንዳይፈታ፣ የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ከማስፈታት ጀምሮ ያሉ የስምምነቱን ሂደቶች በማጓተት ሕዝቡን ለከፋና የተራዘመ መከራ እየዳረገው እንደሆነ አሳውቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ የራያ አማራ ሕዝብ ላይ ወረራ እንደፈፀመ እውቅና እንዲሰጥ እና የማንነት እና ወሰን ጥያቄ የሚነሳባቸውን ቦታዎች ዘላቂ እልባት እንዲሰጣቸው የራያ ወሎ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው የአቋም መግለጫ አሳውቋል።
በሌላ በኩል፣ መላው የአማራ ሕዝብ በህወሓት ወረራ ስር ለወደቀው የራያ አማራ የተለመደው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሲል የማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴው ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ የትግል ጥሪ አስተላልፏል።
ኮሚቴው ህወሓት በራያ አማራዎች ላይ ወረራ ከፈፀመበት ጊዜ አንስቶ ታጣቂዎቹ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት፣ ከአንድ ዓመት በላይ እየተፈፀመ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በአንድነት እንዲያወግዙ ለሀገር ውስጥና ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጥሪውን አቅርቧል።


