Sunday, May 3, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር የሠላም ስምምነት ተፈራርመው የነበሩ ታጣቂዎች መልሰው ማመፃቸው...

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር የሠላም ስምምነት ተፈራርመው የነበሩ ታጣቂዎች መልሰው ማመፃቸው ተሰማ። 

ሐምሌ 7/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትጥቅ ትግል አቁመው ከክልሉ መንግሥት ጋር የሠላም ስምምነት ተፈራርመው የነበሩ ታጣቂዎች ስምምነቱን አፍርሰው መልሰው ትጥቅ ማንሳታቸውን ዞብል ፖስት ከምንጮቹ ሰምቷል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች  ጋር ከፈረንጆቹ 2022 እስከ 2024 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት የሠላም ስምምነት ተፈራርሞ የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ታጣቂዎቹ መልሰው ወደ ግጭት እየገቡ ይገኛሉ።

የክልሉ መንግሥት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ እና የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከሚባሉ ሁለት ታጣቂ ቡድኖች ጋር የጀመረው የሠላም ስምምነት ሂደት፣ ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ 2016 ዓ.ም በስኬት መጠናቀቁን የክልሉ ርዕሰመስተዳድር አቶ አሻድሊ ሁሴን ይፋ አድርገው ነበር።

ከመንግሥት ጋር እርቅ የፈፀሙ የታጣቂ ቡድኖቹ አመራሮች በክልሉ መንግሥት ሥልጣንና መልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ያገኙ ቢሆንም፣ “በስኬት ተጠናቀቀ” ከተባለው የሠላም ስምምነት በኋላ የታጣቂ ቡድኖቹ በርካታ አባላት ሙሉ በሙሉ ትጥቃቸውን እንዳላስረከቡ የሚጠቁሙ መረጃዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲወጡ ነበር።

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር በሱዳን ካርቱም ከሦስት ዓመታት በፊት የሠላም ስምምነት ተፈራርሞ የነበረው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ አባላት፣ ከሰሞኑ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በተለያዩ ቦታዎች ውጊያ ማድረጋቸውን ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል። 

የንቅናቄው ታጣቂዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት መፈፀማቸው የተነገረ ሲሆን፣ በክልሉ የወርቅ ማውጫ አቅራቢያ፣ በቡለን፣ በጉባ፣ እና በማምቡክ አካባቢዎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ውጊያ ማድረጋቸውን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል። 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቤንሻንጉል ሕዝብ ነፃ አውጭ ንቅናቄ መሪ የነበረው አብዱልዋህብ መሐድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ ከሚገኝ እስር ቤት፣ ከሦስት ዓመታት በፊት አምልጦ ወደ ሱዳን መግባቱ የሚታወስ ነው።

የንቅናቄው መሪ የነበረው አብዱልዋህብ ከእስር ካመለጠ በኋላ፣ ከሱዳን ሆኖ ታጣቂዎችን ይመለምል እና ያደራጅ እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎች እንዳሉም ሁኔታውን ለመፅሔታችን ያስረዱ የመረጃ ምንጫችን ገልጸዋል።

ከሰሞኑ የሠላም ስምምነቱን ሽረው ከመንግሥት ጋር ወደ ግጭት የገቡትን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ ታጣቂዎችን ጨምሮ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አራት የተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች ይንቀሳቀሳሉ።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ የጉሙዝ ታጣቂ፣ እንዲሁም ከክልሉ መንግሥት ጋር የተደረገውን የሠላም ስምምነት ያፈረሱት የቤንሻንጉል ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ ታጣቂዎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ እና በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት የሚፈፅሙ ቡድኖች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ባሳለፍነው ግንቦት ወር መጨረሻ ከሱዳን ብሉናይል ግዛት ሰልጥነው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የቤንሻንጉል ተወላጆችን እና አረብኛ ተናጋሪዎችን አጣምሮ የያዘው ቡድን ሌላኛው በክልሉ የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ነው። ይህ ቡድን ከ170 በላይ ሱዳን ውስጥ የሰለጠኑ ታጣቂዎችን ያቀፈ እና በሰኔ ወር አጋማሽ በዓባይ ግድብ አቅራቢያ ጥቃት መፈፀሙን ዞብል ፖስት ዘግቦ ነበር።

የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት በተለያዩ ጊዜያት ከአማፂ እና ታጣቂ ቡድኖች ጋር “የሠላም ስምምነት” ተፈራርመናል እያሉ ቢያስነግሩም፣ ተደረጉ የተባሉት በርካታ ስምምነቶች ከፕሮፓጋንዳ የዘለለ ተጨባጭ ሠላም ማምጣት እንደተሳናቸው ተፈፃሚ ሳይሆኑ እየፈረሱ የሚገኙ የሠላም ስምምነቶች ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች