Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዜናዋና ዋና ዜናየሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሠን ሼክ መሀሙድ እና የቱርኩ አቻቸው ጣይብ ኤርዶጋን ተገናኘተው መከሩ።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሠን ሼክ መሀሙድ እና የቱርኩ አቻቸው ጣይብ ኤርዶጋን ተገናኘተው መከሩ።

ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት የአፍሪካ ቀንድ ዜና! 

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሠን ሼክ መሀሙድ እና የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን በዛሬው ዕለት ተገናኘተው መክረዋል። ሁለቱ መሪዎች ተገናኝተው የተወያዩት በቱርክ አንካራ እንደሆነ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ከአንድ ሰዓት በፊት ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት እንዳለው፣ ሁለቱ መሪዎች በቱርክ እና ሶማሊያ መካከል ያለውን ወንድማማችነት እና የሁለቱን ሀገራት የጋራ ጥቅም በማጠናከር እና ዘላቂ እንዲሆን በማድረግ ዙሪያ ዛሬ በቱርክ አንካራ ተወያይተዋል።

ከዚህ ቀደም ቱርክ የሶማሊያ የውሃ ጠረፍ ጠባቂ እንድትሆን እና በሀገሪቱ የተፈጥሮ ማዕድናትን ለማውጣት የሚያስችላትን ስምምነት ከሶማሊያ ጋር መፈራረሟ የሚታወስ ሲሆን፣ ስምምነቱ የተፈረመው ዐቢይ አህመድ ከሶማሌላንድ ጋር የወደብ መግባቢያ ስምምነት በፈረንጆቹ 2024 መግቢያ ላይ መፈራረማቸውን ተከትሎ ነበር።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሠን ሼክ መሀሙድ ከግብፁ አቻቸው አብዱል ፈታህ ኤልሲሲ ጋር ከአራት ቀናት በፊት በግብፅ ተገናኝተው በሠላምና ፀጥታ፣ በወታደራዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በንግድ ልውውጥ ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያና እና ሶማሌላንድ መካከል ተደርጎ በነበረው የወደብ መግባቢያ ስምምነት ምክንያት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት መሻከሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ሁለቱ ሀገራት በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተደረገውን ውል ወድቅ የሚያደርግ እና ግንኙነቶቻቸውን መልሶ የሚያድስ ስምምነት በቱርክ አንካራ ባሳለፍነው ታሕሳስ ወር መፈራረማቸው ይታወሳል።

ይሁንና የአንካራው ስምምነት የመፈፀም ዕድሉ እየጠበበ መምጣቱን ተከትሎ፣ ሶማሊያ የአጋሮቿን ድጋፍ መልሳ ወደ መፈለግ የዞረችበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ሀሠን ሼክ መሀሙድ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችውን የወደብ መግባቢያ ስምምነት ተከትሎ ከጎናቸው ወደ ቆሙት ግብፅ እና ቱርክ ከሰሞኑ መጓዛቸው የዚሁ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወደ ውጥረት መግባታቸውን ተከትሎ ግብፅ ለሶማሊያ ከአርባ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጓ የሚታወስ ሲሆን፣ ቱርክ በበኩሏ በአንድ በኩል የሶማሊያ የውሃ ጠረፍ ጠባቂ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያንና ሶማሊያን አስታራቂ የሆነችበት ክስተት መፈጠሩ አይዘነጋም።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች