ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት እና የአሁኑ የጠቅላይ ሚንስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በቅርቡ ወደ አሜሪካ ሊጓዙ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ መንግሥታዊ ተልዕኮዎችን ይዘው ወደ አሜሪካ እንደሚሄዱ ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ እሳቸው በሊቀመንበርነት ከሚመሩትና በቅርቡ ከተመሰረተው ስምረት ፓርቲ የውጭ ደጋፊዎች ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሏል።
የአቶ ጌታቸው ረዳ የአሜሪካ ጉዞ በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን በትግራይ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለማወያየት እንዲመስል ተደርጎ የታቀደ መሆኑን በመጠቆም፣ የጉዟቸው ዋነኛ ዓላማ ግን ከአሜሪካ ሴናተሮችና ባለስልጣናት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር ስለመሆኑ የመረጃ ምንጫችን የታቀደውን ጉዞ አስመልክቶ ያደረሱን መረጃ ያሳያል።
የትግራይ ክልል ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት እና የኤርትራ ጉዳይ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ ወደ አሜሪካ ይዘዋቸው የሚሄዱ ሁለት አንገብጋቢና አበይት የመንግሥት ተልዕኮዎች እንደሆኑ፣ ዞብል ፖስት የአቶ ጌታቸውን ጉዞ አስመልክቶ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።
የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት፣ የአሀኑ የጠቅላይ ሚንስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር፣ እንዲሁም የስምረት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከዐቢይ አህመድ የተሰጣቸውን መልዕክት ይዘው በአሜሪካ ከሚገኙት ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሣኤ ጋር በጋራ በመሆን የአሜሪካን ባለስልጣናት አግኝተው እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል።
ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ይደረግባቸዋል ከተባሉ ጉዳዮች መካከል፣ በትግራይ ክልል የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ወደ ጦርነት እንዳያመራ አሜሪካ ጫና እንድትፈጥር ማግባባት አንደኛው እና ቀዳሚው አጀንዳ ነው ተብሏል።
ከህወሓት የወጡ ወታደራዊ መሪዎች እና ታጣቂዎች ያደራጁት “የነፃ መሬት” ወይም የትግራይ ሠላም ሠራዊት የተሰኘው ኃይል እና ነባሩ ህወሓት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ ግጭት መግባታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባሳለፍነው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግርም በትግራይ ክልል አዲስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ እየተሰራ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ከህወሓት በወጡ የትግራይ ልሂቃን ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ ባሳለፍነው ግንቦት ወር እንደተመሰረተ የሚታወስ ሲሆን፣ በአቶ ጌታቸው የሚመራው ስምረት ፓርቲ ከነፃ መሬት ወይም የትግራይ ሠላማዊ ሠራዊት ኃይል ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠቁሙ በርካታ መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ።
አቶ ጌታቸው ረዳ “ከሠላም ይልቅ ጦርነትን ይደግሳል” ብለው ከሚወነጅሉት የእነ ደብረፅዮን ቡድን ይልቅ እሳቸው ያደራጁት እና የሚመሩት ከህወሓት የተገነጠለው ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ይበልጥ እንደሚሻል አሜሪካኖቹን ማግባባት የጉዟቸው አካል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካ ባለስልጣናትን ከአቶ ጌታቸው ጋር ሆነው ያነጋግራሉ የተባሉት ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሣኤ፣ በአፋር ክልል ወታደራዊ ስልጠና እየወሰደ የሚገኘውን “የነፃ መሬት ታጣቂ” ወይም “የትግራይ ሠላም ሠራዊት” በስፍራው ተገኝተው መጎብኘታቸውንና ቀጥሎም ስምረት ፓርቲ በአዲስአበባ ባደረገው ስብሰባ መገኘታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ሌላኛው የአቶ ጌታቸው ረዳ የአሜሪካ ጉዞ ዓላማ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትርነታቸውን የሚመለከት ሲሆን፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን የዲፕሎማሲያዊ ውጥረት አስመልክቶ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን አግኝተው ያስረዳሉ ተብሏል።
አቶ ጌታቸው ረዳን እና ከእሳቸው ጋር የአሜሪካ ባለሥልጣናትን አግኝተው ያነጋግራሉ ተብለው የሚጠበቁትን ጄኔራል ፃድቃንን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ልሂቃን ጥለውት የወጡት ህወሓት፣ ከኤርትራ ጋር ፅምዶ የተሰኘ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጥምረት መፍጠሩ ይታወሳል።
በተለይ በትግራይ እና ኤርትራ የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች የተመሰረተው ፅምዶ የተሰኘው ጥምረት፣ ትግራይን ወደ ሌላ የጦርነት ድግሥ ሊያስገባት እንደሚችል አቶ ጌታቸው ለአሜሪካ ባለሥልጣናት አፅንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአሜሪካውያን ጉዞ አስመልክቶ መረጃውን ያደረሱን ምንጮች አስረድተዋል።
በሌላ በኩል፣ በአሜሪካ የሚኖሩ የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ ደጋፊዎች፣ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ተገናኝተው በትግራይ የፖለቲካ ትኩሳት ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያመላክታል።
ዞብል ፖስት “አቶ ጌታቸው ወደ አሜሪካ ጉዞ የሚያደርጉት መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ ለመረጃ ምንጫችን ያቀረበ ቢሆንም፣ የመረጃ ምንጫችን ቀኑን ከማሳወቅ ተቆጥበዋል።


