ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
የመከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ካውንስል ትኩረቱን በሀገራዊ እና ቀጠናዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያደረገ ስብሰባ ማድረጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወታደራዊ ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የተጠራው የወታደራዊ ካውንስሉ አስቸኳይ ስብሰባ በከፍተኛ የዕልቂት ዋዜማ ላይ ባለው አዳዲስ የሀገር ውስጥና ተሻጋሪ ጦርቶች ላይ ውይይት ለማድረግና ደራሽ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ መሆኑን የዞብል ፖስት ወታደራዊ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት የወታደራዊ ካውንስሉ አንዱ የመወያያ አጀንዳ ሲሆን፣ በያዝነው ሐምሌ ወር የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ ኪሳራ ያደረሰበትን ሽንፈት በአማራ ፋኖ ማስተናገዱ ወታደራዊ ካውንስሉ የክልሉን ሁኔታ በአጀንዳነት ለመምረጥ ዋነኛ አስገዳጅ ምክንያት ነው ተብሏል።
ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ በተደረገ ውጊያ መከላከያ ሠራዊቱ በደጋ ዳሞት ኪሳራ እንደደረሰበት ይታወሳል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ደግሞ በጎንደር በተለያዩ ቀጠናዎች በርካታ የሠራዊቱ አባላት ተገድለዋል፣ በመቶዎች ተማርከዋል፣ የጦር መሳሪያ መካዝኖች ተሰብረው በፋኖ እጅ ገብተዋል እንዲሁም በርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወድመዋል።
ይሄንን ተከትሎ አማራ ክልልን መቆጣጠር የሚችል የአድማ ብተና እና ሚሊሻ አባላትን የክልሉ መንግሥት በብዛት እንዲያሰለጥን በማድረግ “ችግሩን ራሳቸው ይወጡት” በሚል ክልሉን የመከላከያ ሠራዊቱ ለቅቆ እንዲወጣ የሚያስችል ስራ መሰራት አለበት የሚል ሃሳብ በውይይቱ ላይ ተነስቶ እንደነበርም የመረጃ ምንጮቻችን አያይዘው ገልጸዋል።
ሌላኛው የወታደራዊ ካውንስሉ አጀንዳ በህወሓት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ህወሓት ከባድ መሳሪያዎችን ለፌዴራል መንግሥቱ ካለማስረከቡም በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ መሳሪያዎችን መታጠቅ መጀመሩን ወታደራዊ ካውንስሉ በግምገማው አንስቷል።
በብዙዎች ዘንድ “የፌዴራል መንግሥቱ ሆን ብሎ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በታቀደለት ጊዜ እንዳይፈፀም አድርጓል” የሚል ወቀሳ የሚነሳ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ህወሓት መልሶ እንዲያንሰራራ ተጨማሪ እድል ተሰጥቶታል የሚል ቅሬታን የፈጠረ ጭቅጭቅ በስብሰባው ላይ ተነስቷል ተብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ “ህወሀት በፕሪቶሪው ስምምነት መሰረት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲያወርድ የሚለው ስምምነት ተፈፃሚ እንዳይሆነ ፖለቲካዊ አመራሩ ደባ ፈፅሟል” የሚል ሃሳብ በካውንስሉ አባላት መነሳቱንና “ስምምነቱን ቀድመን ማስፈፀም ነበረብን” የሚል በቃላት ውርዋሮ የታጀበ ግምገማ እና ሂስ ተካሂዶ እንደነበርም ወታደራዊ ምንጮች አክለው ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ፊልድ ማርሻሉ የህወሓት አቅም ላይ የግምገማ እንጅ የውሳኔ ችግር እንዳልነበረ በመጥቀስ፣ “የህወሓት ወታደራዊ ኃይልና የጦር መሳሪያ አቅም ከዛው ከጎረቤቶቻቸው ጋር መናቆሪያ እንጅ የፌደራል መንግስቱን ዳግም ለመውጋት የሚያበቃ አይደለም” የሚል ግምገማ ነበረን ብለዋል፡፡ በዚህም የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲጓተትና ለዚህ እንዲበቃ ያደረገን ስሁት ግምገማችን ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ትጥቅ ሊፈታ እና ወደ ማሕበረሰቡ መልሶ ሊቀላቀል የሚገባው የህወሓት ሠራዊት በታንክ እና በአየር መቃወሚያ የታገዘ አዲስ ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ፣ ተጨማሪ አባላትን በመመልመል እና ለጦርነት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ከትግራይ ክልል የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከወታደራዊ ካውንስሉ መወያያ አጀንዳዎች መካከል ሌላኛው ጉዳይ ኤርትራን የሚመለከት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው የግንኙነት መሻከር ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል ሲሉ ብዙዎች ግምታቸውን ያጋራሉ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ወደ ድንበር ማስጠጋቱን የሚጠቁሙ መረጃ በመውጣት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በአሰብ በኩል ደግሞ የአየር መቃወሚያ መትከሉ ተነግሯል። ኢትዮጵያ ባንፃሩ፣ በአፋር በኩል በሚያዋስነው እና ቡሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባሳለፍነው ወር የአየር ላይ ቅኝት ማድረጓንና ሜካይዝድ ጦሩን ያካተተ ከፍተኛ ሀይል ማስጠጋቷ ተነግሯል።
እነዚህ እና መሰል ሁኔታዎች ወታደራዊ ካውንስሉ የኤርትራን ጉዳይ አስመልክቶ ላደረገው ግምገማ ገፊ ምክንያት ናቸው ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ በኤርትራ እና በህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች መካከል የተፈጠረው “ፅምዶ” የተሰኘው ጥምረትም ኤርትራን የተመለከተው ሌላኛው የውይይት አጀንዳ ተደርጎ ተነስቷል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን የተመለከተ ግምገማ የተደረገ ሲሆን፣ ጃል ሰኚን በድርድር ማስገባት ከቻልን ወዲህ በጃል መሮ የሚመራው ታጣቂ ኃይል በክልሉ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተስፋፍቶ መቀጠሉን እና በፌዴራል እና የኦሮሚያ የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ወታደራዊ ካውንስሉ በስብሰባው ገምግሟል ተብሏል።


