Tuesday, May 5, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየአማራ ማኅበር በአሜሪካ የአማራ አንድነት ግንባር በአስቸኳይ እንዲፈጠር ጥሪ አቀረበ።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የአማራ አንድነት ግንባር በአስቸኳይ እንዲፈጠር ጥሪ አቀረበ።

ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም-ዞብል ፖስት ዜና! 

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በዐቢይ አህመድ መንግሥት፣ ህወሓት እና ሌሎች ተዋናዮች መካከል ወደ ጦርነት ሊያመራ የሚችል ውጥረት መከሰቱን በመጥቀስ፣ ሁኔታው ባለፉት አራት አመታት በጦርነት ውስጥ እያለፈ እና የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት ባለው የአማራ ሕዝብ ላይ ሊያደርስ የሚችለው መዘዝ እንዳሳሰበው ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ማኅበሩ ከዚህ ቀደም በነበረው የሰሜኑ ጦርነት ህወሓት ከኦነግ ጋር ጥምረት መፍጠሩን በማስታወስ፣ ቡድኑ የአማራ እና የአፋር ግዛቶችን በስፋት መውረሩን እና ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በላይ የአማራ ተወላጆች የተገደሉበትን የማይካድራ ጭፍጨፋ ጨምሮ በርካታ የዓለም አቀፍ ወንጀሎች መፈፀሙን በመግለጫው አስታውሷል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ አያይዞ፣ የሰሜኑን ጦርነት ለመቋጨት የተደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት አማራን የጦርነት አውድማ እንዳደረገው እንዲሁም ህወሓት በፌዴራል መንግሥቱ ታግዞ በስድስቱ የራያ ወረዳዎች ወረራ እና የዘር ማፅዳት መፈፀሙን አብራርቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ህወሓት ወደ ወልቃይት፣ ሰቲት ሑመራ፣ እንደ ጠለምት ባሉ የሰሜን ጎንደር ግዛቶች፣ እንዲሁም በሰሜን ወሎ እና ዋግህምራ ግዛቶች ጦሩን በማንቀሳቀስ ለዳግም ወረራ መዘጋጀቱን የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ አማራን ለሁለንተናዊ ጥቃት የዳረጉትን የፖለቲካ ኃይሎችን ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች በመገምገም፣ የአማራ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እና የሲቪል ቡድኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ አንድ እንዲመጡ ጥሪውን አቅርቧል።

ዐቢይ አህመድ በአማራ ሕዝብ ላይ ያወጀው ጦርነት ሁለት ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ አማራን ከጭቆና እና ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ነፃ ለማውጣት የትጥቅ ትግል የጀመረው ፋኖ በርካታ ወታደራዊ ድሎችን ከማግኘት ባሻገር ፖለቲካዊ አንድነትን መፍጠር ተስኖት በአንድ የዕዝ ጠገግ ውስጥ መግባት ግን አልቻለም።

ለዚህም በርካታ ጉዳዮች እንደምክንያት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በፋኖ አመራሮች እና አደረጃጀቶች የተከሰቱ አለመግባባቶች፣ በአማራው ጠላቶች ዙሪያ በልሂቃኑ መካከል የጋራ መግባባት አለመኖር፣ እንዲሁም የተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶች የሚጣረሱ ፍላጎቶች ካሏቸው የዳያስፖራ ማኅበራት እና ግለሰቦች ጋር ያላቸው ግንኙነት የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች ወደ አንድ እንዳይመጡ ያደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ በርካቶች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይስተዋላል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው ውጥረት እንዳሳሰበው በመጠቆም፣ የአማራ ልሂቃን፣ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ማኅበራት፣ እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት እየታዩ ላሉ ለውጦች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ እና አስቸኳይ የአማራ አንድነት ግንባር ለመመስረት መስራት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥቶ ገልጿል። 

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች