Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዘገባዎችአራት ኪሎወታደራዊ አመራሮች "በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ጦርነቶችን በአግባቡ አልመራችሁም" ተብለው በጅጅጋ ወታደራዊ እስር ቤት...

ወታደራዊ አመራሮች “በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ጦርነቶችን በአግባቡ አልመራችሁም” ተብለው በጅጅጋ ወታደራዊ እስር ቤት እየታሰሩ ነው።

ነሐሴ 5/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና! 

የዐቢይ አህመድ መንግሥት በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች እያካሄደ የሚገኘውን ጦርነት በአግባቡ አልመሩም ያላቸውን የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች በወታደራዊ እስር ቤቶች እያሰረ እንደሚገኝ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።

በወታደራዊ እስር ቤቶች እንዲታሰሩ እየተደረጉ የሚገኙት ወታደራዊ መሪዎች፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከፋኖ እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር እየተካሄዱ የሚገኙ ጦርነቶችን በአግባቡ አልመራችሁም በሚል እንደሆነ ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ጦርነቶችን እንዲመሩ የተመደቡ ወታደራዊ መሪዎች እየታሰሩ የሚገኘው በሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ወታደራዊ እስር ቤት መሆኑን መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ጠቅሰዋል።

ወታደራዊ አመራሮቹ ለእስር ተዳርገዋል የተባለው በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር እየተደረጉ ባሉ ጦርነቶች፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ የሰው እና የቁሳዊ ውድመት እንዲደርስበት አድርገዋል በሚል መሆኑን የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት ፋኖን አዳክመናል፣ የመለቃቀም ስራ ነው የቀረን፣ የአማራ ክልልን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ጥቂት አካባቢዎች ብቻ ነው የቀሩን ሲሉ የሚደመጡ ቢሆንም፣ ዛሬም ድረስ ፋኖ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ብርቱ ውጊያ በማድረግ ላይ ይገኛል። 

በጅጅጋ ወታደራዊ እስር ቤት ታስረዋል ከተባሉት ወታደራዊ አመራሮች መካከል፣ ካሳለፍነው ሐምሌ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል ከፍተኛ ወታደራዊ ኪሳራን ያስተናገዱ አመራሮች እንደሚገኙበት የመረጃ ምንጫችን አያይዘው ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁለት ዓመታት በፊት ፋኖን ትደግፋላችሁ ተብለው የታሰሩ በርካታ ወታደራዊ መኮንንኖች መኖራቸውን እና ወታደራዊ አመራሮቹ ከታሰሩባቸው ቦታዎች መካከል ጅጅጋ የሚገኘው ወታደራዊ እስር ቤት አንዱ መሆኑን ከዚህ በፊት በሰራነው የምርመራ ዘገባ ማጋለጣችን አይዘነጋም።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች